ቀጥታ፡

ኢንስቲትዩቱ በ107 ሚሊዮን ብር ወጪ የጀመረው የህንፃ ማስፋፊያ ግንባታ በመቋረጡ ለብልሽትና ኪሳራ እየተዳረገ ነው

አዲስ አበባ ሀምሌ 19/2010 የኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት በ107 ሚሊዮን ብር አጠቃላይ ወጪ በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ የጀመራቸው የህንጻ ግንባታዎች ከሁለት ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ ተቋርጠው ለብልሽት አየተዳረጉ መሆናቸው ተነገረ። የሰልጣኞች መኝታ ክፍሎችን ጨምሮ  የተለያዩ አገልግሎት መስጫዎችን የሚያካትተው የግንባታ ፕሮጀክቱ  የተጀመረው በ2006 ዓ.ም ሲሆን ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ተጠናቆ ለታለመለት ዓላማ መዋል ነበረበት። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በደረሰው ጥቆማ መሠረት በስፍራው ባደረገው ምልከታና ባገኘው መረጃ መሰረት የግንባታው 85 በመቶ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ ተቋርጦ ሁለት ዓመት አስቆጥሯል፤ በዚህም የተነሳ 69 ሚሊዮን ብር የወጣበት የአስካሁኑ የግንባታ ሥራ ለጥፋትና ኪሳራ ተዳርጓል። ኢዜአ ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የድርጅቱ ሠራተኞች አንደሚሉት ግንባታው ከሁለት ዓመት በፊት ሲጀመር የተያዘለት በጀት 107 ሚሊዮን ብር  ሲሆን ለእስካሁኑ ሥራ 69 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፤ ግንባታው በመጓተቱ የተነሳም ቀሪ ሥራውን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ 80 ሚሊዮን ብር ተጠይቋል። የማስፋፊያ ህንጻዎቹ ግንባታ ፕሮጀክት ከጅምሩ ውስብስብ ችግሮች ያሉበት መሆኑንም ሰራተኞቹ በማስራጃ ያስረዳሉ። ለአብነትም የግንባታው ጨረታ ሲወጣ በኢንስቲትዩቱ የተወከሉት የኮሚቴ አባላት የተዋቀሩት ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ በመሆኑ ገና ከጅምሩ ሆን ተብሎ የታሰበ ህገ ወጥ ተግባር መኖሩን ይናገራሉ። ምንም እንኳ የኢንስቲትዩቱ ሂሳብ ኦዲት ባለመደረጉ የተነሳ በወቅቱ የሚፈለገው ብድር ማግኘት ያልቻለ ቢሆንም ያለውን ኃብት ተጠቅሞ ግን የህንፃዎቹን ቀሪ ሥራ ማጠናቀቅ ይቻል እንደነበርም ሠራተኞቹ ይገልፃሉ። የኢዜአ ሪፖርተር መገንዘብ አንደቻለው እስካሁን የተከናወኑት ግንባታዎች በተወሰነ መልኩ ለብልሽት እየተዳረጉ ናቸው፤ ጡቦችንና ሲሚንቶዎችን ጨምሮ የተለያዩ የግንባታ ግብዓቶችም በየቦታው ተዝረክርከው ለብክነት ተዳርገዋል። ሰራተኞቹ ሌሎች ችግሮችንም ይገልፃሉ። እነርሱ እንደሚሉት ኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉበት። ተቋሙ የሠራተኞች መብትና ጥቅም የሚጣስበት፣ የመንግስት ኃብት በስፋት የሚባክንበት ነው። በመሆኑም የሚመለከተው የመንግስት አካል አስፋላጊውን እርምጃ እንዲወሰድም አሳስበዋል። የማስፋፊያ ህንጻዎቹ የሰልጣኞች ዶርም፣ የማስልጠኛ ክፍሎች፣ ዳቦ መጋገሪያ፣ ጋራዥና የፍሳሽ ማስወገጃዎች ጨምሮ 11 ፕሮጀክቶችን ያካተተ ነው። በኢትዮጵያ ሥራ አመራር ኢንስቲትዩት የቢሾፍቱ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጁ አቶ ክበበው ጣፋ በተቋሙ ኃላፊ ሆነው የመጡት የህንፃዎቹ ግንባታ ከቆመ በኋላ መሆኑን ጠቅሰው ግንባታዎቹ በጊዜ ባለመጠናቀቃቸው ተቋሙ ለተጨማሪ ወጪ እየተዳረገ ነው ይላሉ። ወደ ተቋሙ የሚገቡ ሰልጣኞች በአሁኑ ወቅት የሚያርፉት ሆቴሎችን በመከራየት መሆኑን የሚናገሩት አቶ ክበበው በዚህም ቅርንጫፍ ማሰልጠኛ ተቋሙ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአማካይ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ለአልጋ ኪራይ ወጪ አድርጓል ብለዋል። የፕሮጀክቱ ግንባታ በጊዜው ተጠናቆ ቢሆን ግን ይህንን ከፍተኛ ወጪ ማዳን ይቻል ነበር ሲሉም ያብራራሉ። ግንባታው የተቋረጠው ሥራውን ለማስጨረስ የሚያስችል ብድር ከንግድ ባንክ ማግኘት ባለመቻሉ እንደሆነ ነው አቶ ክበበው የሚገልፁት። ኢዜአ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ለቀድሞ ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ እና ለንግድ ባንክ የተጻፉ የብድር ጥያቄ ደብዳቤዎችን ተመልክቷል። አቶ ክበበው ስራ አስኪያጅ ሆነው ከተመደቡ ጀምሮ 'ተቋሙ ለምን ብድር ተከለከለ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ ኢንስቲትዩቱ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ኦዲት ባለመደረጉ የተነሳ ነው ይላሉ። የህንጻዎቹ ግንባታ አማካሪ የሆነው ሀብታሙ ኢንተርናሽናል የአርክቴክቶች ማህበር ሥራ አስኪያጅ አርክቴክት ሀብታሙ ኃይለማሪያምም ይህንኑ አረጋግጠዋል።  ''ኢንስቲትዩቱ ብድር ማግኘት አልቻልኩም በማለቱ ግንባታው እንዲቋረጥ ተደርጓል'' ነው ያሉት። በዚህም የተነሳ አማካሪ ኩባንያው ማግኘት የነበረበትን ክፍያ ያጣ ከመሆኑም በላይ ስሙም እንዲጎድፍ ሆኗል ሲሉም  አቶ ሀብታሙ ቅሬታቸውን ገልፀዋል። የተቋረጠው ግንባታ አሁን ባለበት ከቀጠለ የአስካሁኑ ሥራ ሙሉ በሙሉ ለብልሸትና ለብክነት መዳረጉ የማይቀር በመሆኑ ጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው አንደሚገባም ነው ሥራ አሰኪያጁ የሚናገሩት። ከላይ ከተጠቀሱት መረጃዎች መረዳት የሚቻለው ኢንስቲትዩቱ ግንባታውን ሲያቅድ 30 በመቶ ከተቋም በጀት 70 በመቶውን ደግሞ በብድር ለመሸፈን አቅዶ የነበረ ቢሆንም 85 በመቶ የሚሆነውን ግንባታ በ30 በመቶ ማከናወን መቻሉን ነው። ይህ አውነታም አብዛኛውን ሥራ በራሱ በጀት መሸፈን ከቻለ አሁን እየደረሰ ያለውን ጥፋት ለመታደግ ለምን ቀሪውን 15 በመቶ ግንባታ ማስጨረስ አቃተው የሚል ጥያቄ ያጭራል። በዚህና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የተቋሙን የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ ለማግኘት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር የኢንስቲትዩቱን ዋና ዳይሬክተር ለማግኘት በተደጋጋሚ ሞክሮ አልተሳካለትም። ምክትል ዳይሬክተሩ ደግሞ "ለተቋሙ አዲስ ነኝ" በማለታቸው ምላሽ መስጠት አልቻሉም። የሆነው ሆኖ ግን ኢዜአ ኃላፊዎቹ በተገኙበት ወቅት አስትያየታቸውን ለመቀበል ዝግጁ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም