ቀጥታ፡

ማህበሩ የእናቶችና ጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ ጥረቱን እንዲያጠናክር ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 9/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ኃኪሞች ማህበር የእናቶችና ጨቅላ ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል የጤና ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ።

29ኛው የኢትዮጵያ የጽንስና ማህፀን ኃኪሞች ማህበር ዓመታዊ ጉባኤ "በስነ-ተዋልዶ፣ እናቶች፣ ጨቅላ ህፃናት፣ ህፃናትና ወጣቶች ላይ የኮቪድ-19  ተፅዕኖን መቀነስ" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ይገኛል።

ጉባኤው ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ኮቪድ-19 በእናቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ላይ ባለው ተፅዕኖና ባለሙያዎች ይህንን ተቋቁመው ማከናወን በሚገባቸው ተግባራት ላይ አተኩሮ ይመክራል ተብሏል።  

ማህበሩ በስነተዋልዶ፣ በእናቶችና ህፃናት ጤና ላይ ጥናት በማድረግና የተለያዩ መመሪያዎችን በማዘጋጀት የጤና ሚኒስቴርን ሲያግዝ መቆየቱን የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ድጉማ ተናግረዋል።

ማህበሩ ለባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት በኩል ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም እነዚህን ተግባራት ሊያጠናክር እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኮቪድ-19 መከሰትን ተከትሎ ለወሊድ አገልግሎት ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡ እናቶች ቁጥር ቀንሶ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ደረጄ፣  ችግሩን ለመፍታት ሚኒስቴሩ ከማህበሩና ሌሎች አጋሮች ጋር በሰራው ሥራ ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም ማህበሩ ይህንን ሥራ ከማጠናከር ባለፈ የእናቶችንና የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ ተግቶ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።

ሚኒስቴሩ የጨቅላ ህፃናትን ሞት ለመቀነስ "የህፃናትን ህይወት እንታደግ" የሚል ኢኒሼቲቭ ለመተግበር ማቀዱንም ገልፀዋል።

ለእናቶች ሞት መቀነስ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት መካከል ወሳኝ የሆነውን የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ለማስፋትም ማህበሩ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እንዲሰራም አመልክተዋል።

ዶክተር ደረጄ የእናቶችና ህፃናት ሞት ምጣኔን አሁን ካለበት በተሻለ ለመቀነስ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር መቅደስ ዳባ እንዳሉት ማህበሩ ላለፉት 29 ዓመታት በእናቶችና ስነ-ተዋልዶ ጤና እንዲሁም በጨቅላ ህጻናትና ህፃናት ላይ ለፖሊሲ ግብአት የሚሆኑ የተለያዩ ጥናቶችን አካሂዷል።  

በዘርፉ የስፔሻሊቲ ስልጠና የሚሰጡ 13 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መኖራቸውን ገልጸው፣ ማህበሩ የስፔሻሊቲ ስልጠና በሚሰጥባቸው ተቋማት እየተማሩ ያሉ ባለሙያዎችን ለማብቃት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የትምህርት ተቋማቱ ለሚሰጡት ስፔሻላይዝድ ስልጠና ስታንዳርድ ማዘጋጀቱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቷ ገለጻ ማህበሩ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በስድስት ክልሎች ቅርንጫፍ ያለው ሲሆን፣ ይህም በየአካባቢው በባለሙያዎች የታገዘ የክህሎት ስልጠና ለመስጠት አስችሎታል።

ለስልጠናው በክልል ያሉ 15 ሆስፒታሎች የተለዩ ሲሆን በቅርቡም በ11ዱ ስልጠና መሰጠቱን ገልፀዋል።

"ማህበሩ በእናቶችና ህፃናት እንዲሁም በስነተዋልዶ ጤና ላይ እያደረገ ያለውን አስተዋፅኦ በቀጣይም አጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል ዶክተር መቅደስ ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም