ኢዜአ የአገልግሎት አድማሱን ሊያሰፋ እንደሚገባ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ የአገልግሎት አድማሱን ሊያሰፋ እንደሚገባ ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 9/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሁሉንም ለመድረስና ተጨማሪ ደንበኞችን ለማፍራት የአገልግሎት አድማሱን ሊያሰፋ እንደሚገባ ተጠቆመ።
ተቋሙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ባለባቸው አገራት ቅርጫፍ በመክፈት ተደራሽነቱን ማስፋት እንደሚችል ተመላክቷል።
ኢዜአ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ጋር በመሆን የመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጡ አዋጆችና የዜና አገልግሎት ዓለም አቀፍ ፋይዳና ተሞክሮ በሚል ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ትናንት በአዳማ ተካሄዷል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት መምህር ዶክተር ተሻገር ሽፈራው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በ1990 ዓ.ም በአፍሪካ ከሚገኙ የዜና አገልግሎት ተቋማት በዋነኛነት ይጠቀስ እንደነበር ገልጸዋል።
በወቅቱ የኢንተርኔት መምጣት፣ የመገናኛ ብዙሃን መስፋፋትና የዜና አገልግሎት ስራዎች ከመጋረጃ በስተጀርባ ያሉና ለሰዎች እይታ ቅርብ ባለመሆናቸው በአፍሪካ የዜና አገልግሎቶች ወደ መዘጋት መግባታቸውን አስታውሰዋል።
በዚህ ውጣ ውረድ ውስጥ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጎልቶ በመውጣት ስራዎችን ሲያከናውን ቢቆይም በተለያዩ የመንግስት ስርዓቶች አንዴ እየፈረሰ በሌላ ጊዜ እንደገና እንዲቋቋም መደረጉ ተቋሙን እንዳዳከመው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች ከ30 በላይ ቅርንጫፎች እንዳሉት የገለጹት ዶክተር ተሻገር ቅርንጫፎቹን በመጨመርና አቅሙን በማጎልበት ተደራሽነቱን ማስፋት ከቻለ ትልቅ ሙያዊ አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ስራዎች የደንበኞቹን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ እንዳላት ብዝሃነት ዜና አገልግሎት አሁን መረጃ የሚያቀርብባቸውን ቋንቋዎች መጨመር እንዳለበትም ተናግረዋል።
ተቋሙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ባለባቸው አገራት ቅርጫፍ በመክፈት ተደራሽነቱን ማስፋትና ዓለም አቀፋዊ ሚናውን መወጣት እንደሚችልም አመልክተዋል።
የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ማኅበረሰቡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ስራዎችን እንዲረዳ ራሱን የማስተዋወቅና ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ማከናወን እንዳለበት ገልፀዋል።
ተቋሙ የተለያዩ የመረጃ ማሰራጫ አማራጮችን ቢጠቀም ተደራሽነቱን ማስፋት ይችላል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ ተቋሙ በ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱ ተደራሽነቱን ማስፋትና ዓለም አቀፍ ሚናውን መወጣት እንዲችል በሌሎች አገራት ቅርንጫፍ መክፈት ትኩረት እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።
አገልግሎት የሚሰጥባቸውን ቋንቋዎችን ማሳደግ የስትራቴጂክ ዕቅዱ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢዜአ የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ ለመፈጸም የውስጥ አቅም ግንባታና ለስራዎቹ የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ሟማላት የሚያስችሉትን ተግባራት እያከናወነ ነው ብለዋል።
ይሁንና ለስራዎቹ የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶችና ግብዓቶች ለማሟላት የግዢ ሂደት አሰራሮች ቀልጣፋ ሊሆኑ እንደሚገባና ለሚያስፈልገው ግዢም የመንግስትን ድጋፍ እንደሚፈልግ አመልክተዋል።
ድርጅቱን እንደገና ለማቋቋም በመወጣው አዋጅ የብሮድካስትና የሕትመት አገልግሎቶች ላይ በመሰማራት አድማሱን ለማስፋት እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በመገናኛ ብዙሃን መስክ መንግስት ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ከለያቸው ዘርፎች አንዱ የዜና አገልግሎት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ መንግስት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሚያስፈልገውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለማስተዋወቅ እየሰራ ያለው ስራ መልካም የሚባል እንደሆነና ይህንኑ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገነዝበዋል።