የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ተፈጻሚ አልሆነም - የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ - ኢዜአ አማርኛ
የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ተፈጻሚ አልሆነም - የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ

የካቲት 9/2013 (ኢዜአ) የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው አዋጅ ተፈጻሚ መሆን እንዳልጀመረ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከብሮድካስት ባለስልጣን ጋር በመሆን የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ፣ የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው አዋጅ እንዲሁም የዜና አገልግሎት ዓለም አቀፍ ፋይዳና ተሞክሮ በሚል የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ትናንት በአዳማ ተካሄዷል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየካቲት 2012 ዓ.ም የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ ማፅደቁ ይታወሳል።
ይሁንና አዋጁ እስካሁን ተፈጻሚ ሲሆን አልታየም፣ በአዋጁ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን የሚጥሱ ድርጊቶች እየተፈጸሙ እርምጃ እየተወሰደ አይደለም፣ ወደ ፍርድ ቤትም ጉዳዮች እየመጡ አይደለም ? የሚሉ ጥያቄዎች በውይይቱ ተሳታፊዎች ተነስተዋል።
የጥላቻ ንግግር ትርጓሜ ለተለያየ አተረጓጎም የተጋለጠ ነው ይሄም ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ ሁኔታ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር አይችልም ወይ? የሚል ጥያቄም ከተሳታፊዎች ተነስቷል።
የመገናኛ ብዙሃን አዋጅን በተመለከተም አንድ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ድርጅትና ግለሰብ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ውስጥ 25 በመቶ ድርሻ እንዲይዝ መደረጉ ተወዳዳሪነት ላይ ተጽዕኖ አያሳድርም ወይ? የመገናኛ ብዙሃንን አደረጃጀት በአክሲዮን ላይ የተመሰረተ አያደርገውም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችም ቀርበዋል።
የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ በላይሁን ይርጋ የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው አዋጅ እስካሁን ተፈጻሚ ያልሆነው በቅድሚያ ስለ አዋጁ ግንዛቤ መፍጠር በማስፈለጉ ነው ብለዋል።
በአዋጁ ዙሪያ የግንዛቤና የስርጸት ስራ ሊጀመር በታሰበበት ጊዜ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከሰቱ ግንዘቤ የመፍጠር ስራው ሊሳካ አለመቻሉን አስረድተዋል።
በክልሎች በአዋጁ የሕግ ጥሰት የተፈጸመባቸውን ጉዳዮች የመመርመርና አንዳንዶቹን ወደ ፍርድ ቤት የመውሰድ ሁኔታ ቢኖርም ቅድሚያ ማስተማር አስፈላጊ በመሆኑ ጉዳዮቹ እንዲያዙ መደረጋቸውንና የግንዛቤ ስራዎችን በስፋት በማከናወን አዋጁ በፍጥነት ተፈጻሚ እንዲሆን እንደሚደረግ ነው አቶ በላይሁን ያስረዱት።
የጥላቻ ንግግር ትርጓሜ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችና ተግባራትን ከግምት ያስገባና አስፈላጊው ትርጓሜ ላይ ጥንቃቄ የተደረገበት በመሆኑ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ ተጽዕኖ እንደማያሳድር ተናግረዋል።
የጥላቻ ንግግርና የሀሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከል የወጣው አዋጅ 'የጸረ-ሽብር አዋጅን የተካ ነው' የሚለው ሀሳብ ትክክል እንዳልሆነና አዋጁ በመናገር ነጻነት ላይ ገደብ እንዳልጣለም ገልጸዋል።
የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ አርቃቂ ቡድን ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ጎሹ በበኩላቸው በአዋጁ የተቀመጠው የመገናኛ ብዙሃን የባለቤትነት ድርሻ ክፍፍል ተደራራቢ ባለቤትነት ወይም ጠቅላይነትን ለማስቀረት ዓላማ ያለው እንጂ በመገናኛ ብዙሃን ተወዳዳሪነት ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር እንዳልሆነ አብራርተዋል።
የድርሻ ክፍፍሉ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑንም አክለው የባለቤትነት ጉዳይ መሰረቱን ያደረገው የገበያ ድርሻን እንጂ በአክሲዮን ሽያጭ ላይ የተመሰረተ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
የሕትመት መገናኛ ብዙሃን ለማበረታት በዘርፉ ያሉ ተቋማት መዋሐድ እንዲችሉና በአዋጁ በገበያ ድርሻ ግዢ ላይ ገደብ እንዳልተጣለባቸው አመልክተዋል።
ነገር ግን በአንድ የብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን 25 በመቶ ድርሻ ያለው አንድ ድርጅት ወይም ግለሰብ የሌላን ብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን የገበያ ድርሻ ጠቅልሎ መግዛት ሲፈልግ በዚህ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን እንደሚሆን ነው አቶ ሰለሞን ያብራሩት።
ይሄም የሆነበት ምክንያት ብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን ካላቸው ባህርይ፣የካፒታል ወጪና አሰራር አንጻር ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በአንድ መገናኛ ብዙሃን ውስጥ ከ25 በመቶ የማይበልጥ ድርሻ እንደሚኖራቸው በአዋጁ መደንገጉን ገልጸው ነገር ግን ፈቃድ አውጥተው መስራት እንደማይችሉ አክለዋል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ ሁለቱ አዋጆች መንግስት በተለያዩ መስኮች ባደረጋቸው ማሻሻያዎች ለመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት ያሳያሉ ብለዋል።
ለአዋጆቹ ከዝግጅት እስከ ማፅደቅ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው ወደ ስራ እንዲገቡ ላደረጉ ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋና አቅርበዋል።