ቀጥታ፡

የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ለልማት ስራዎች 600 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ ነው

የካቲት 9/2013 (ኢዜአ) የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በኢትዮጵያ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ለማከናወን የ600 ሚሊዮን ብር በጀት መድቦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገለፀ።

ድርጅቱ በጀቱን የመደበው በ2013/2014 በጀት ዓመት በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚያከናውናቸው የልማት ስራዎች መሆኑን አስታውቋል።

የጤና ሚኒስቴር ኮቪድ-19ን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት ለማገዝ ከ102 ሺህ ዮሮ በላይ ወጪ የተደረገባቸው የሕክምና ቁሳቁስ ለመለገስ መዘጋጀቱን ገልጿል።

የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተጠሪ አቶ ይልማ ታዬ እንዳሉት በጀቱ ለግብርናና ተፈጥሮ ሃብትና ለውሃ ልማት፣ ለትምህርት፣ ለጤና፣ ለቤተሰብ ምጣኔ፣ ለኤች.አይ.ቪ/ኤዲስ/ ፕሮግራም፣ ለሰው ሃብት ልማት፣ ለስራ ዕድል ፈጠራና ለተቀናጀ የገጠር መሰረተ ልማት ግንባታ ይውላል።

በዚህም በተቀናጁ የገጠር ልማት ስራዎች ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማት ፕሮጀክቶች ተቀርጸው እንደሚከናወኑ አስታውቀዋል።

የተለያዩ የአቅም ግንባታ ማጎልበቻ ስልጠናዎችም ይሰጣሉ ብለዋል።

የድርጅቱ የቦርድ ዳይሬክቶሬት አባል ዶክተር ሳባስቲያን ብራንዲስ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ ከ25 ሺህ 200 በላይ ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስምንት አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ለመስራትና ግንባታቸው የተጀመሩ 20 ትምህርት ቤቶችን ለማጠናቀቅ መታቀዱን ተናግረዋል።

ድርጅቱ ለ637 ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ማቀዱንና ከ90 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የውሃ ስራዎችን እንደሚያከናውን ተገልጿል።

የጤናውን ዘርፍ ለመደገፍ ለ38 ሺህ ህጻናትና ለ129 ሺህ ሴቶች በወረዳ ደረጃ በሽታ ተከላካይ የክትባት አገልግሎት እንዲያገኙም ይደረጋል።

በቤተሰብ ምጣኔና ስነ-ተዋልዶ ከ137 ሺህ በላይ ሴቶችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ አስፈላጊው የገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚደረግ ተነግሯል።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አንኮበር ወረዳ በ24 ቀበሌዎችና በኦሮሚያ ምዕራብ ሸዋ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተቀናጀ የገጠር ልማት ስራዎች እንደሚከናወኑም ተመላክቷል።

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን አምስት ወረዳዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ሰፊ የቡና ልማት ፕሮጀክት በመቅረፅ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉም ተነግሯል።

እነዚህ አርሶ አደሮች 400 ኩንታል ቡና በማምረት ወደ ጀርመን ለመላክ ዝግጅት መጨረሳቸውም ተጠቁሟል።

ድርጅቱ በተጨማሪም መተከልን ጨምሮ በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ለተፈናቀሉ ዜጎች ሠብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ የመንግስትን ምላሽ እየጠበቀ መሆኑ ተጠቁሟል።

እ.አ.አ. 1980 በዶክተር ካርል ሄንዝ በም የተመሰረተው የሰዎች ለሰዎች ግብረ ሰናይ ድርጅት በኢትዮጵያ ለ40 ዓመታት ሠብዓዊ ተግባራት እያከናወነ የሚገኝ ዓለምዓቀፍ ድርጅት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም