ቀጥታ፡

የአድዋ ጀግኖች ያቆዮዋትን ነፃ ሀገር ወጣቱ ትውልድ ሊጠብቅ ይገባል..የአርበኞች ማህበር አባላት

ሐዋሳ የካቲት 9/2013 (ኢዜአ) የአድዋ ጀግኖች ፍፁም በሆነ መንፈሳዊ ፅናት በዱር በገደል ተዋግተው ያቆዮዋትን ነፃ ሀገር ወጣቱ ትውልድ ሊጠብቅ ይገባል ሲሉ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞ ማህበር አባላት አስገነዘቡ።

  በማህበሩ የደቡብ ቅርንጫፍ ሊቀመንበር የኃላሸት ቸርነት በሰጡት አስተያየት የአድዋ ድል ለኢትዮጵያዊያን ነጻነትና ኩራትን ያጎናጸፈ ነው።

ድሉ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች በቅኝ ግዛት ለነበሩት ሀገራት ሁሉ የነፃነት ተምሳሌት መሆኑን ተናግረዋል።

"ትውልዱ ከዚህ አኩሪ ታሪክ በመማር በተሰማራበት መስክ ጠንክሮ ከመስራት ጎን ለጎን የጥንት አባቶች በህይወት መስዋዕትነት ያቆዩለትን ነፃ ሀገር ከጠላት ሊጠብቅ ይገባል" ብለዋል።

በተለይ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍና ተሳትፎ በማጠናከርና ከግብ በማድረስ የአባቶችን ፈለግ እንዲከተል ጥሪ አቅርበዋል።

የማህበሩ ዋና ጸሐፊ ወይዘሮ የሺ ለማ በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያን  በዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀውን የጣሊያን ሠራዊት ሊያሸንፉት የቻሉት ሃገርን አላስደፍርም የሚል ጠንካራ አቋም፣አንድነትና ፍቅር በመያዝ መሆኑን አመልክተዋል ።

"ዛሬም የኢትዮጵያ ጠላቶች አያንቀላፉም" ያሉት ጸሐፊዋ ትውልዱ የጠላትን  ሴራ  በመገንዘብ የሀገሩን ዳር ድንበር ሊያስከበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

"የአርበኞች ቀንን ሥናስብ ታሪኩን በማንሳት ለተተኪው ትውልድ በማስተማር ጭምር ሊሆን ይገባል" ያሉት ደግሞ  የማህበሩ አባል ወይዘሮ አማከለች መኩሪያ ናቸው።

ድሉ በባርነት ቀንበር የተጋዙ ጥቁር ህዝቦችን የዘመናት ጭቆናና የስነ-ልቦና ስብራት  የጠገነና ተስፋን የፈነጠቀ መሆኑን  ተናግረዋል።

"አሁን ላይ ወጣቱ ትውልድ ሃገራዊ ማንነትን እያጠፋ በመጣው መጤ ባህል ተገዢ ከመሆንና በማህበራዊ ሚዲያ ከመነቆር ተቆጥቦ ልክ እንደ አድዋ ድል ለልማት ሊተባበር ይገባል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም