የአንድነትና የአብሮነት መገለጫ ከሆነው የዓድዋ ድል ኅብረትና መተሳሰብን ልንማር ይገባል -- የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአንድነትና የአብሮነት መገለጫ ከሆነው የዓድዋ ድል ኅብረትና መተሳሰብን ልንማር ይገባል -- የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች
የካቲት 8/2013 (ኢዜአ) የአንድነትና የአብሮነት መገለጫ ከሆነው የዓድዋ ድል ሕብረትና መተሳሰብን መማር እንደሚገባ የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች ተናገሩ።
የአድዋ ድልን አስመልክተው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የዩኒቨርሲቲው ተመራቂዎች ድሉ ኢትዮጵያዊያን አንድነትና ሕብረታቸውን አጠንክረው በመንቀሳቀሳቸው የተገኘ ውጤት ነው ይላሉ፡፡
የአድዋ ድል የኢትጵያዊያን ብቻ ሳይሆን ጥቁር አፍሪካዊያን የሚኮሩበት ጭምር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ድሉ ከአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት የመጡ አባትና እናት አርበኞች በከፈሉት መስዋዕትነት የተገኘ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን አብሮነታቸውን በማጠናከር ማክበር እንዳለባቸው ነው ምሩቃኑ የተናገሩት።
የኢትጵያዊያን የአንድነት መገለጫና የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ከሆነው የዓድዋ ድል ሕብረትና መተሳሰብን መማር እንደሚገባም ነው የገለጹት።
ጀግኖች አባቶች ተባብረው በመንቀሳቀሳቸው ባገኙት ድል የአገር ሉአላዊነት እንዳስጠበቁ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም አንድነቱን በማጠናከር ድህነትና ጸረ-ሠላም ኃይሎችን ድል ለመንሳት መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።
አድዋ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ውጤት መሆኑን የገለጹት ተመራቂዎቹ የትናንቱን የድል ታሪክ ዛሬ ለመድገም ትውልዱ በውስጡ ያለውን አሉታዊ አመለካከትና እርስ በእርስ መገፋፋት መተው እንዳለበትም ተናግረዋል።
እርስ በእርሱ በመደጋገፍና በመተባባር ኢትዮጵያን ወደፊት ማራመድና ልማቷን ማስቀጠል ይኖርብናል ሲሉም አስተያታቸውን ሰጥተዋል።
የአድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን ድል ብቻ ሳይሆን መላው አፍሪካ የሚኮራበት ድል መሆኑም ይታወቃል፡፡
የአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ለስምንተኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 576 ተማሪዎች በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ማስመረቁ ይታወቃል፡፡