ቀጥታ፡

ለፀረ-አበረታች ቅመሞች ምርመራ የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ ለመቀነስ እየተሰራ ነው

የካቲት 8/2013 (ኢዜአ) ለፀረ-አበረታች ቅመሞች ምርመራ የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ ለመቀነስ በሀገር ውስጥ ላቦራቶሪ ለማቋቋም ጥናት እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ጽሕፈት ቤት ገለፀ።

የጽህፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል በየዓመቱ ለፀረ አበረታች ምርመራ የሚመደበው ወጪ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር መሆኑን ተናግረዋል።

እ.አ.አ ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች ቅመሞች ተቋም አባል መሆኗንና በተያዘው ዓመት ለፀረ አበረታች ቅመሞች ምርመራ እንዲሆን 21 ሚሊዮን ብር መመደቧን ገልፀዋል።

አገሪቷ በየዓመቱ ለፀረ-አበረታች ቅመሞች ምርመራ የምታወጣው ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ በአገር ውስጥ ላቦራቶሪ ለማቋቋም ጥናት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ላቦራቶሪው ዓለም አቀፉ የፀረ አበረታች ቅመሞች ተቋም ባወጣው መመዘኛ መስፈርት የሚቋቋም መሆኑን እንዲሁ። 

ጥናቱ ሲካሄድ ለፀረ አበረታች ቅመሞች ምርመራ የሚያገልግሉ ሆስፒታሎችን በአገር ውስጥ ለይቶ ለመንግሥት በማቅረብ በጀት እንዲመደብ የማድረግ ሥራ እንደሚከናወንም አስታውቀዋል።

የተሻለ መሠረተ ልማት ያላቸውን ሆስፒታሎች አወዳድሮ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ ከዜሮ ተነስቶ ግንባታ ለማከናወን የሚወስደውን ጊዜ እንደሚቆጥብም ነው አቶ መኮንን ያስረዱት።

ላቦራቶሪውን የመክፈቱ ሂደት በፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ዕቅድ ጭምር መካተቱንና ለተግባራዊነቱም በትብብር ለመስራት መታሰቡን አክለዋል።

እንደ አቶ መኮንን ገለጻ በኢትዮጵያ የፀረ አበረታች ቅመሞች ምርመራ በሰባት የስፖርት ዓይነቶች ላይ ለማድረግ ጥረት ቢደረግም ወጪው ከፍተኛ በመሆኑ ምርመራው በአትሌቲክስና በእግር ኳስ ብቻ ተወስኗል።

"ላቦራቶሪውን በሀገር ውስጥ መክፈት ከተቻለ ችግሩ ስለሚፈታ በሌሎች የስፖርት አይነቶችም ምርመራውን ማድረግ ይቻላል" ብለዋል።

በሌላ በኩል ስለ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ግንዛቤ የሚሰጥ ሰነድ በትምህርት ሥርዓት ውስጥ እንዲካተት እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

ይዘቱን በተመለከተ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር እየተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ መኮንን በጽህፈት ቤቱ የ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድም ስለ ፀረ አበረታች ቅመሞች ግንዛቤ የሚሰጥ ሰነድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

"ለአትሌቶች ወይም ለስፖርት ባለሙያዎች ለተወሰኑ ቀናት ሥልጠና በመስጠት ዘለቄታዊ መፍትሄ ማምጣት አይቻልም" ያሉት ዳይሬክተሩ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ከተካተተ ከግንዛቤ ባለፈ ሰዎች የሕይወት ዘይቤያቸው ሊያደርጉት እንደሚችሉ አስረድተዋል።

በመሆኑም ከ5ኛ ክፍል ጀምሮ የፀረ አበረታች ቅመሞች ሕጉ በስፖርት ትምህርት ውስጥ ተካቶ ለተማሪዎች ግንዛቤያቸውን የማሳደግ ስራ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም