ሰማሪታንስ ፐርስ በትግራይ ድጋፍ ለሚሹ ወገኞች ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ዓልሚ ምግብ አበረከተ - ኢዜአ አማርኛ
ሰማሪታንስ ፐርስ በትግራይ ድጋፍ ለሚሹ ወገኞች ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ዓልሚ ምግብ አበረከተ
የካቲት 8/2013 (ኢዜአ) ሰማሪታንስ ፐርስ የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት በትግራይ ክልል ሠብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ዓልሚ ምግብ አደረሰ፡፡
ግብረ ሰናይ ድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤቱ ከሚገኝበት ኖርዝ ካሮላይና ግዛት ቡን ከተማ በራሱ የዕቃ ጫኝ አውሮፕላን የላከው የምግብ ቁሳቁስ ዛሬ መቀሌ አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ ደርሶ ተራግፏል፡፡
የሰማሪታንስ ፐርስ የኢትዮጵያ ተወካይ ኒክ ቤካርት ድርጅቱ ዋና መስሪያ ቤቱ ከሚገኝበት ኖርዝ ካሮላይና ግዛት የላከው ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ዓልሚ ምግብ መሆኑን ገልፀዋል።
በትግራይ ክልል በሕግ ማስከበር ሂደቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ህጻናት፣ ለነፍሰጡር እና ለሚያጠቡ እናቶች የሚውል ከ310 ኩንታል በላይ ዓልሚ ምግብ ነው።
መቀሌ የደረሰው ሰብዓዊ ድጋፉ ለ18 ሺህ ህጻናት እና እናቶች ለአንድ ወር የሚበቃ ነው ብለዋል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ አበበ ገብረህይወት ከግብረ ሰናይ ድርጅቱ የተገኙት አልሚ ምግቦች ለህጻናትና ለአረጋዊያን እንደሚውል ገልፀዋል።
ለሰማሪታንስ ፐርስ ግብረ ሰናይ ድርጅትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
አቶ አበበ እስካሁን በትግራይ ክልል 2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሕዝብ ሠብዓዊ ድጋፍ ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡
ድጋፉ የተሟላ ይዘት ያላቸው ምግቦች የተካተቱበት በመሆኑ ጠቃሚ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅት አመራሮች በመቀሌ ከተማ ተገኝተው በክልሉ እየተሰጠ ባለው ሠብዓዊ ድጋፉ ዙሪያ ከጊዜያዊ አስተደደሩ ጋር ተወያይተዋል፡፡
የሠብዓዊ ድጋፍ አሰጣጡ ጥንካሬዎችና ጉድለቶች ላይ ውይይት ማካሄዳቸውን የጊዜያዊ አስተዳዳሩ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ አበበ ገብረህይወት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
በትግራይ ክልል እየተሰጠ ያለው ሠብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡