ቀጥታ፡

የገጠር ከተሞችን ከፀሃይ ሃይል የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ተፈረመ

የካቲት 8 /2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 25 የገጠር ከተሞችን ከፀሀይ ሃይል ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ስምምነት ከሶስት የቻይናና ከአንድ የኮሪያ ኩባንያዎች ጋር ተፈራረመ።

ስምምነቱን የፈረሙት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሺፈራው ተሊላና የኩባንያዎቹ ተወካዮች ናቸው።

ፕሮጀክቱ በስምንት ክልሎች በተመረጡ የገጠር ከተሞች የሚከናወንና ከ145 ሺህ በላይ ዜጎችን የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

ግንባታው ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ 20 ሚሊዮን ዶላርና ከኢትዮጵያ መንግስት በሚሸፈን 161 ሚሊዮን ብር ነው የሚከወን ነው።

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ስምምነቱ ሲፈረም በሁሉም የአገሪቷ ክፍሎች ተመጣጣኝ የሃይል አቅርቦት እንዲኖር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ስምምነቱ የተደረሰበት ፕሮጀክትም ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር /ግሪድ/ በርቀት ላይ የሚገኙ አካባቢዎችን ከፀሃይ ሃይል ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል።

ሚኒስትሩ ፕሮጀክቱ በስድስት ወራት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

የፕሮጀከቱ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ስምንት ሜጋዋት ሃይል ማመንጨት እንደሚችል ተገልጿል።

እንዲሁም 68 ነጥብ 7 መካከለኛ እና 233 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ዝቅተኛ የመስመር ዝርጋታም ይሸፍናል ተብሏል።

ለግንባታው መፋጠን የአካባቢው ነዋሪዎችና አመራሮች ድጋፍ እንዲያደርጉ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሺፈራው በበኩላቸው አምና ከተጀመሩ 12 የፀሃይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ስምንቱ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውንና ቀሪዎቹም በቅርቡ እንደሚጠናቀቁ አክለዋል።

በአጠቃላይ በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ብቻ 125 አዳዲስ የገጠር መንደሮችን የሃይል ጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

የቻይናዎቹ ኩባንያዎች ተወካዩ ሚስተር ኪው ቺንግዣን የአገራቸው ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት ስራዎች መሳተፋቸውን አንስተዋል።

በዚህ የተገኘው ልምድም የአሁኑን ስምምነት በፍጥነትና በጥራት ለመስራት ያግዛል ብለዋል።

ፕሮጀክቶቹን በተያዘው የጊዜ ገደብ አጠናቆ ለማስረከብ ቁርጠኛ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም