ቀጥታ፡

የመንግሥት ድጎማ መጠበቅና ገቢን በአግባቡ አለመጠቀም ስፖርቱን እየጎዳው ነው - ስፖርት ኮሚሽን

አዲስ አበባ፣ የካቲት 8/2013 ( ኢዜአ)  የመንግሥትን ድጎማ መጠበቅና የፋይናንስ ገቢን በአግባቡ ጥቅም ላይ አለማዋል የስፖርቱን ዘርፍ እየጎዳው መሆኑን ስፖርት ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በ10 ዓመት የስፖርት መሪ የልማት ዕቅዱ ላይ ከስፖርት ጋዜጠኞች ጋር መክሯል።

የኮሚሽነሩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሠለሞን አልዩ የፌዴሬሽኖችና የክለቦች የበጀት መጠን አነስተኛ መሆኑን በዚሁ ጊዜ ገልፀዋል።

በበጀቱ ማነስ ሳቢያ በመንግሥት ድጎማ ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውም ስፖርቱን ማዳከሙን ተናግረዋል። 

የስፖርት ማኅበራት የተስተካከለ የፋይናንስና የቁጥጥር ሥርዓት ስለሌላቸው ገንዘብ ቢኖራቸውም በአግባቡ ባለመጠቀማቸው ስፖርቱን መደገፍ እንዳልቻሉ ነው የጠቆሙት።

የቁጥጥርና የኦዲት ሥርዓት ስላልተዘረጋላቸውም የገንዘብ ብክነት ሲታይ ትክክል አይደለም ብሎ ማረም አልተቻለም ነው ያሉት።

በመሆኑም ከመንግሥት የሚለቀቅ ድጎማ መጠበቅና ገቢን በአግባቡ አለመጠቀም የስፖርቱን ዘርፍ እየጎዳው እንደሆነ ነው አቶ ሠለሞን ያስታወቁት።

ይሁንና ኮሚሸኑ ይፋ ባደረገው የ10 ዓመት የስፖርት መሪ የልማት ዕቅድ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችና የኦዲት ሥርዓቶችን በመዘርጋት ችግሩን ለማስተካከል መታሰቡን ጠቁመዋል።

"በውጭ አገራት የገንዘብ አጠቃቀማቸውን የሚያሳይ መረጃ በድረ ገፃቸው በመልቀቅ የኦዲት ሪፖርት ያደርጋሉ" ያሉት አቶ ሠሎሞን ይህን አይነት የቁጥጥር ዘዴ እንደ አንድ ስልት ለመጠቀም ታስቧል ብለዋል።

በመንግሥት ድጋፍ ያለውን ስፖርት ባለሀብቱ እንዲሳተፍበት በማድረግ ፌዴሬሽኖች፣ ክለቦችና የስፖርት ማኅበራት በገንዘብ ራሳቸውን ችለው እንዲንቀሳቀሱ እንደሚሰራም ገልጸዋል።

ባለሀብቶች ከስፖርት ማኅበራት ጋር ግንኙነት በመፍጠር ራሳቸውን ጠቅመው ስፖርተኞችን እንዲያፈሩ ለማድረግ መታሰቡንም አቶ ሰለሞን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን የማስተላለፍ መብት ለዲ.ኤስ.ቲቪ በመስጠት እግር ኳሱን የማስተዋወቅ ሥራ እንደተሰራ ሁሉ በሌሎች የስፖርት ዘርፎችም ይኸው ሥራ ይከናወናል ብለዋል። 

በተጨማሪም በኀብረተሰቡ ተሳትፎ የሚገነቡ የማዘውተሪያ ሥፍራዎች ላይ አተኩሮ ለመስራት መታሰቡን ነው አቶ ሠለሞን ለኢዜአ የገለጹት።

ይህም ኅብረተሰቡ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማውና በአብዛኛው በመንግስት ድጋፍ እየተንቀሳቀሰ ያለውን የስፖርት ዘርፍ ለመደገፍ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

ራሱን የቻለ የማኅበረሰብ ስፖርት ተሳትፎ ዳይሬክቶሬት በመፍጠር ወደ ክልል፣ ዞን እና ወረዳዎች የሚወርድ መዋቅር መሰራቱን ጠቁመዋል።

እንደ ማስስፖርት ያለ ኅብረተሰቡን በሰፊው የሚያሳትፍ ስፖርት የራሱ ሕግና ደንብ ወጥቶለት በዚህ ዳይሬክቶሬት ውስጥ እንዲካተት እንደሚደረግም ተናግረዋል።

የማኅበረሰብ ስፖርትን ለማሳደግ የዓለም አቀፍ ተሞክሮን ከመውሰድ ባሻገር በአካል ብቃት ፕሮግራም የተለያዩ አደረጃጀቶች ለመፍጠር መታሰቡንም ገልፀዋል።


እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ ኮሚሽኑ በቀጣዩ የ10 ዓመት መሪ ዕቅዱ የስፖርት ዘርፉን የማስፈፀም አቅም ለመገንባት፣ የስፖርት መሠረተ ልማቶችን ለማስፋፋትና የኅብረተሰብ ተሳትፎን ለማጎልበት ይሰራል።

በተለይ የትምህርትና ሥልጠና መርሃ ግብሮችን ማጠናከር፣ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ማጎልበትና ስፖርትን ለማኅበራዊ ልማትና ለአገር ብልፅግና ለማዋል ታስቧልም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም