ቀጥታ፡

መንግሥት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው ህልፈተ ህይወት የተሰማውን ሃዘን ገለጸ

አዲስ አበባ  ሀምሌ19/2010 የኢፌዴሪ መንግሥት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ድንገተኛ ህልፈተ-ህይወት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን ገለጸ። የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ኢንጂነር ስመኘው የግድቡ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ከተመደቡበት ጊዜ አንስቶ ለአገራቸው እና ለህዝባቸው ያላቸውን ፍቅር በተግባር የገለጹ ናቸው። የአገር ፍቅርን ለወገኖቻቸው በተግባር ያስተማሩ፣ ከፍተኛ መስዋዕትነትን የከፈሉ፣ የዜግነትና የሙያ ግዴታቸውን በአርዓያነት የተወጡ  የልማት አርበኛ መሆናቸውን መግለጫው አመልክቷል። ኢንጂነር ስመኘው በኢትዮጵያውን ልብ ውስጥ ለዘላለም ሲታወሱ የሚኖሩ ታላቅ አገር ወዳድና ባለውለታ እንደሆኑ ተጠቅሷል። የኢፌዴሪ መንግሥት በእኚህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ አገር ወዳድ ህልፈተ-ህይወት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለጸ፣ ለቤተሰቦቻቸው እና ለመላው ኢትዮጵያውያን መጽናናትን ተመኝቷል። የህዳሴ ግድቡ ዋና ስራ አስኪያጅ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት ኢንጂነር ስመኘው ዛሬ ረፋድ ላይ በመስቀል አደባባይ መኪና ውስጥ ሞተው መገኘታቸው ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም