ቱርክ በኢትዮጵያ በተጨማሪ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት አቅዳለች- የቱርክ አምባሳደር - ኢዜአ አማርኛ
ቱርክ በኢትዮጵያ በተጨማሪ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት አቅዳለች- የቱርክ አምባሳደር
የካቲት 8/2013 (ኢዜአ) ቱርክ በኢትዮጵያ ባላት ኢንቨስትመንት ላይ በተጨማሪ ዘርፎች ለመሰማራት እንደምታቅድ በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ያፕራቅ አልፕ ገለጹ።
አምባሳደር ያፕራቅ ቱርክ በኢትዮጵያ የምታደርገውን የኢንቨስትመንት ስራ ማስፋት ትፈልጋለች ነው ያሉት።
የቱርክ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በጨርቃጨርቅ ፤በኬብል አምራችነት እና ሌሎች ዘርፎች ተሰማርተዋል።
በኢትዮጵያ ፈሰስ በማድረግ የሀገሪቱ ባለሃብቶች ከቻይናውያን በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
የቱርክ ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ የአናዶሉ ኤጀንሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡
ቱርክ እና ኢትዮጵያ ረጅም አመታት ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የዚሁ ጠንካራ ግንኙነት አካል የሆነ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ወደ ቱርክ እንደሚያቀኑ ተነግሯል፡፡
አቶ ደመቀ መኮንን በቱርክ በሚኖራቸው ቆይታ ከሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በሁለትዮሽ፣ በቀጠናዊ እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሏል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በቆይታቸው በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ የተገነባውን አዲሱን የኢትዮጵያ ኤምባሲ መርቀው እንደሚከፍቱ ይጠበቃል፡፡