የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ በተለያዩ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ በተለያዩ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመረቀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7/2013 ( ኢዜአ) የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ በተለያዩ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን ከስድስት ሺህ በላይ ተማሪዎች ዛሬ አስመረቀ።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ዘርፈሽዋል ንጉሴ ተገኝተዋል።
በዛሬው እለት የተመረቁት 6 ሺህ 891 ተማሪዎች የ2012 ዓ.ም ተመራቂዎች ሲሆኑ በ2013 ዓ.ም የወሰዱትን የማካካሻ ስልጠና ያጠናቀቁ መሆናቸው ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጋቱ ዳኛቸው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ''ዘርፉ አገራችን ለተያያዘችው ግስጋሴና አገር በቀል በሆነው የኢኮኖሚ ሪፎርም ውስጥ ትልቅ ሚና አለው''።
''ወጣትነት ማለት ሁሉን ለማድረግ የሚቻልበት ጊዜ በመሆኑ በተሰጣችሁ ጊዜ በዘርፉ የሚጠበቀውን ውጤት ለማምጣት መስራት ይገባችኋል'' በማለት ከዚህ ቀደም ''በጠቅላይ ሚኒስትሩ ''ስለወጣቶች አቅም የተባለውን ለተመራቂዎች አጋርተዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው ዘርፉ አገሪቷ ከድህነት ለመውጣት በምታደርገው ጥረት ውስጥ ድርሻው የላቀ እንደሆነ አንስተዋል።
''መዲናዋ ብዙ ደሃ ማህበረሰብ ይዛለች'' ያሉት ኃላፊው የመካከለኛ እውቀትና ክህሎት ትኩረት ተሰጥቶት ከተሰራ መለወጥ ይቻላል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ''ለሚሰሩ እጆች ሳይሆን ለሚናገሩ አፎች '' ትኩረት ተደርጎ ቆይቷል በማለት "አሁን ለሚሰሩ እጆች ትኩረት ስለተሰጠ በዘርፉ ያላችሁት ውጤታማ ስራ ለመስራት መትጋት ይገባችኋል" ብለዋል።
በእለቱ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የማዕረግ ተመራቂ የሆኑ ተማሪዎች በተመረቁበት የሙያ ዘርፍ አገራቸውን ለማገልገል ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የተያያዘችውን የልማት ጉዞ እውን ለማድረግ ብሎም በ10 አመቱ መሪ የልማት እቅድ ውስጥ ሚናቸውን ለመወጣትና ''የኢትዮጵያ ትንሳኤ አብሳሪዎች ለመሆን እንሰራለን'' ነው ያሉት።
ተመራቂ ተማሪዎች በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን ፣ በሆቴልና ቱሪዝም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፣ በአውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ፣ በቢዝነስና ኤስቴቲክስ ዘርፍ ስልጠና የወሰዱ ናቸው።
ከተመራቂዎቹ መካከል 2 ሺህ 371ዱ ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል።