ቀጥታ፡

እንደ አድዋ ጀግኖች በሀገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ በአንድነት እንቆማለን...የሀዋሳና አካባቢው ነዋሪዎች

ሀዋሳ፣ የካቲት 07/2013 (ኢዜአ) ጀግኖች አባቶቻችን የጣሊያን ወራሪ ኃይል በመመከት በአድዋ ላይ ድል እንደተጎናጸፉ ሀሉ በሕዳሴ ግድብ ግንባታና በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ላይ በአንድነት እንቆማለን ሲሉ የሀዋሳና አካባቢው ነዋሪዎች አስታወቁ።

ከሀዋሳ ነዋሪዎች መካከል አቶ ዘላለም ለገሰ ለኢዜአ እንደገለጹት ጀግኖች አባቶቻችን ለቅኝ ገዢዎች እጅ አንሰጥም በማለት ያስመዘገቡት ድል ጥቁር ህዝቦችን ለነጻነታቸው እንዲታገሉ አነሳስቷል።

"በታላቅ መስዋእትነት የተገኘውን የአደዋ ድል የአሁኑ ትውልድ ሁሌም በማስታወስ ሊዘክረው ይገባል" ብለዋል።

የጥንት አባቶቻችን በተባበረ ክንድ ወራሪውን የጣሊያን ጦር ድል ባይነሱት ኖሮ አሁን የተጎናጸፍነውን ባህል፣ ወግ፣ እምነትና ሌሎች መገለጫዎቻችን ማግኘት ያዳግት እንደነበር ተናግረዋል።

በተለይ የአፍሪካዊያን ነፃ የመውጣት ህልም መክኖ የሚቀርበት እድል ሰፊ ሊሆን እንደሚችል እንዲሁ ጠቅሰዋል።

"አሁን ላይ እየተፈታተኑን ያሉትን  ልዩነቶች ወደ ጎን በመተው እንደ አባቶቻችን ለሀገር ህልውናና ሰላም በአንድነት ዘብ መቆም ይጠበቅብናል " ብለዋል።

በመገባደድ ላይ ያለውን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከዳር ለማድረስና የግብፅና የሱዳንን እኩይ እንቅስቃሴ ለመመከት  መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

አቶ ካሳ ዱባለ በበኩላቸው በጁንታው ህወሓት አገዛዝ ሀገራዊ አንድነትን ከማጠናከር ይልቅ ለመከፋፈል ሲሰራ በመቆየቱ በሀገር ፍቅር ላይ የመሸርሸር አደጋ ተጋርጦ እንደነበር አስታውሰዋል።

"አሁን የተገኘውን የነጻነት አየር በመጠቀም እንደ ጥንት አባቶቻችን በሀገር ጉዳይ ላይ የፀና አቋም በመያዝ አንድነታችንን ልናጠናክር ይገባል"  ብለዋል።

የአደዋ ጀግኖችን የአይበገሬነት አሻራ ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ አስፈላጊ መሆኑን የተናገረው ደግሞ ወጣት ኢያሱ ጎበዛየሁ ነው።

"ዘረኝነት፣ጎጠኝነትና መከፋፈል ለአሁኑ ትውልድ ያልጠቀመ፣ ለመጪውም ክፉ ጠባሳን አኑሮ የሚያልፍ ስለሆነ አጥብቀን ልንታገለው ይገባል" ብሏል ፡፡

የሀገር ሽማግሌ ኑሬ ኑካ  በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያን ወራሪውን የጣሊያን ጦር ማሸነፍ የቻሉት እርስ በእርሳቸው መስማማት በመቻላቸው እንደሆነ አስገንዝበዋል።

"ከዚህ ወሳኝ ከሆነው ትብብር ልምድ በመቅሰም በአንድነት ከቆምን የጋራ ጠላታችንን መመከት እንችላለን" ሲሉ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም