ቀጥታ፡

የአዞ ምርቶችን በሚፈለገው ደረጃ ለገበያ ማቅረብ አልተቻለም ... የአርባ ምንጭ አዞ እርባታ ጣቢያ

የካቲት 7/2013 (ኢዜአ) በገበያ ትስስር ችግር የአዞ ምርቶችን በሚፈለገው ደረጃ ለገበያ ማቅረብ አለመቻሉን የአርባ ምንጭ አዞ እርባታ ጣቢያ አስታወቀ።

በደቡብ ክልል አርባ ምንጭ ከተማ የሚገኘው የአርባ ምንጭ አዞ እርባታ ጣቢያ በ1976 ዓ.ም የተመሰረተና  የአዞ እርድ በማከናወን ቆዳና ስጋ ወደ ውጭ ሲልክ ቆይቷል።     

የጣቢያው ጽህፈት ቤት መረጃ እንደሚያመለክተውም ከ1983 እስከ 1992 ዓ.ም ድረስ 11 ሺህ ቆዳ ለዓለም ገበያ ቀርቧል።     

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ወንደሙ አባተ እንደተናገሩት፤ ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ ምርቱ ለዓለም ገበያ ያልቀረበው የገበያ ትስስር በሚፈለገው ደረጃ ባለመኖሩ ነው ብለዋል።    

ኃላፊው እንደሚሉት፤ በ2010 ዓ.ም ለምርት የደረሱ 1ሺህ500 አዞዎች የገበያ ትስስር ባለመፈጠሩ ታርደው ቆዳቸው እንዲቀመጥ ተደርጓል።      

በየዓመቱ እስከ ሁለት ሺህ የአዞ ቆዳ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ እቅድ ቢያዝም በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ እቅዱን ማከናወን አለመቻሉንም አብራርተዋል።      

እንደ አቶ ወንድሙ ገለጻ ከገበያ ትስስር ችግር ባለፈ የበጀት እጥረትና የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን በዘርፉ የሚያሳትፍ አሰራር አለመኖር ላለው ማነቆ ተጠቃሽ ናቸው።    

አንድ ሳንቲሜትር የአዞ ቆዳ እስከ አምስት ዶላር፣ አንድ ኪሎግራም ስጋ ደግሞ 20 ዶላር ድረስ እንደሚሸጥ ጠቅሰው፤ ለጉዳዩ ትኩረት ባለመሰጠቱ ገቢ እያጣን ነው ብለዋል።    

ከአባያና ጫሞ ሃይቆች በየዓመቱ እስከ 11 ሺህ የአዞ ጫጩቶች ለመሰብሰብ የሚያስችል አቅም መኖሩን የተናገሩት ኃላፊው ዘመናዊ አሰራርን በመተግበር የሚጠበቀውን ገቢ ለማግኘት መሰራት እንዳለበት አመልክተዋል።        

ጣቢያው የቱሪስቶችን ቆይታ ለማሳደግ የእንስሳት መኖሪያ ለመስራት ከሃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ጋር ስምምነት መደረሱን ገልጸው፤ የሰጎንና ጥርኝ እርባታ እንደሚካሄድም ጠቅሰዋል።   

በቀጣይም የአገር ውስጥ የቆዳ አምራቾች ስለ አዞ ቆዳ ግንዛቤ እንዲወስዱ በማድረግ ወደ ምርት እንዲገቡ  ጣቢያው ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።  

የአርባምንጭ አዞ እርባታ ጣቢያው ኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ በፊት በዓመት በአማካይ ከ800 እስከ አንድ ሺህ ድረስ የውጭ አገር ቱሪስቶች ይጎበኙት ነበር።    

በተመሳሳይ ከ30 እስከ 40 ሺህ የሚሆኑ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ከኮቪድ በፊት ይጎበኙት ነበር።

በዚህም በየዓመቱ በአማካይ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ይገኝ እንደነበር የጽህፈት ቤቱ መረጃ ይጠቁማል።  

የቫይረሱን መከሰት ተከትሎ የጎብኚዎች ቁጥር የቀነሰ ሲሆን የተገኘው ገቢም 700 ሺህ ብር ብቻ መሆኑን ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም