አየር መንገዱ ኢትዮጵያዊ ቃና ያላቸውና በተፈጥሮ የበለፀጉ ምግቦችን በበረራዎቹ ለደንበኞቹ ማቅረብ መጀመሩን ይፋ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
አየር መንገዱ ኢትዮጵያዊ ቃና ያላቸውና በተፈጥሮ የበለፀጉ ምግቦችን በበረራዎቹ ለደንበኞቹ ማቅረብ መጀመሩን ይፋ አደረገ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 7/2013 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሁሉም በረራዎቹ ኢትዮጵያዊ ቃና ያላቸውና በተፈጥሮ የበለፀጉ ምግቦች ለደንበኞቹ ማቅረብ መጀመሩን ይፋ አደረገ።
አየር መንገዱ የኢትዮጵያ ተፈጥሮዊ ምግቦች የሚያስተዋውቅበት “በኢትዮጵያ አየር መንገድ ይብረሩ ተፈጥሯዊ ማዕድ ይቋደሱ” የተሰኘ ዘመቻን በይፋ አስጀምሯል።
ትላንት ምሽት በስካይ ላይት ሆቴል በተደረገ ይፋዊ ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያምን ጨምሮ፣ አምባሳደሮች፣ የመንግስት ስራ ሃላፊዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
አየር መንገዱ ከዚህ በፊት ወደ ተለያዩ አገራት ለሚያጓጉዛቸው መንገደኞች ምግቦችን ከተለያዩ አገራት በማስገባት ፍላጎቱን ይሸፍን ነበር።
አሁን ግን አየር መንገዱ በሚያደርጋቸው በረራዎች ኢትዮጵያዊ ቃና ያላቸው በተፈጥሮ የበለፀጉ ምግቦች ማለትም ከስጋ፣ ቆጮ፣ ኑግ፣ ጤፍ እና ከአትክልትና ፍራፍሬ የሚዘጋጁ ምግቦችን ጨምሮ ለጤና ተስማሚ የሆኑ መጠጦች እንደሚያቀርብ አስታውቋል።
ይህ መሆኑ ደግሞ ተፈጥሮዊ ምግቦች የሚመረቱባት ኢትዮጵያ ገጽታዋን በሚገባ ለዓለም እንድታስተዋውቅ እና አየር መንገዱንም በተወሰነ ደረጃ ምግብ ለማስገባት የሚያወጣውን ወጪ እንደሚታደግ ነው የተገለፀው።
ምግቦቹ ብቃታቸው ከተረጋገጠ የአገር ውስጥ አቅራቢዎች የሚቀርብ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በግብርና ምርቶች ለተሰማሩ ሰዎች ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ እድል እንደሚፈጥር ተነስቷል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ኢትዮጵያዊ ቃና ያላቸው በተፈጥሮ የበለፀጉ ምግቦች ለደንበኞች በበረራ ወቅት እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ በተፈጥሮ መንገድ የምታመርታቸው የግብርና ምርቶች ለተጓዦች በማስተዋወቅ በዓለም ገበያ ተፈላጊነታቸው እንዲጨምር በማድረግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲፈጠር ማድረግ እንደሚቻል አንስተዋል።
አየር መንገዱ ከአርሶ አደሮች ህብረት ስራ ማህበራት ጋር በትብብር እንደሚሰራ የተናገሩት አቶ ተወልደ በተለይ አዲስ አበባና ዙሪያዋ ያሉ አርሶ አደሮችና የግብርና ምርት አቅራቢዎች ከዚህ በይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
ከ10 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እንዳሉት የሚነገርለት አየር መንገዱ ኢትዮጵያዊ ቃና ያላቸውና በተፈጥሮ የበለፀጉ ምግቦችን ለደንበኞቹ ማቅረብ መጀመሩ የኢትዮጵያ ምግቦች በመላው አለም እንዲታወቁና አለም አቀፍ ፍላጎት እንዲጨምር ከማድረጉም በላይ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ነው የተገለጸው።
አየር መንገዱ በዓመት ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ለምግብና መጠጥ ግዢ የሚያወጣ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነውን ከውጪ የሚያስገባቸው ምግቦች ይሸፍናሉ።
ኢትዮጵያዊ ቃና ያላቸውና በተፈጥሮ የበለፀጉ ምግቦችን በበረራ ወቅት ማቅረብ መጀመሩን ተከትሎ 10 በመቶ ብቻ ድርሻ ያለውን የአገር ውስጥ ምግቦች ግዢ ወደ 25 በመቶ ከፍ ለማድረግ መታሰቡ ተጠቁሟል።