ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት- ወይዘሮ ሚስራ አብደላ - ኢዜአ አማርኛ
ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት- ወይዘሮ ሚስራ አብደላ
ሃረር፣ የካቲት 7/2013(ኢዜአ) የአንድነትና የትብብር ማሳያ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማጠናቀቅ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የሀረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ ገለጹ።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በክልሉ በሚኖረው የአምስት ወራት ቆይታ 20 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን የክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡
በጽሕፈት ቤቱ የህዳሴው ዋንጫ ህዝባዊ ተሳትፎ ንቅናቄን ለማስጀመርና ለአመራሮች በተዘጋጀ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ላይ የተገኙት ምክትል ርዕሰ-መስተዳድሯ እንዳሉት ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ ጋር ተያይዞ በሚከናወኑ ተግባራት ገቢን ከመሰብሰብ ባለፈ የህዝቡ የኔነት ስሜት እንዲጠናከር ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
“በክልሉ ባለፉት 10 ዓመታት የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም መልካም ተሞክሮዎችን በማጎልበትና ክፍተቶችን በማስተካከል ውጤታማ ተግባራት ለማከናወን ርብርብ ይደረጋል” ብለዋል፡፡
ዋንጫው በየወረዳው ለ10 ቀናት ቆይታ እንደሚኖረው የጠቆሙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ በዚህም የሚከናወኑ ስራዎች በየቀኑ እንደሚገመገሙ አመላክተዋል፡፡
“በተለይም የወረዳ አመራሩ የሀይማኖት አባቶችን የሀገር ሽማግሌዎችን እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎችን ከጎኑ በማሰለፍ እና ህዝብን በማሳተፍ የአንድነትና የመተሳሰብ መገለጫ የሆነውን ግድብ እንዲጠናቀቅ በትኩረት መንቀሳቀስ ይገባል” ብለዋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሔራዊ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍቅርተ ታምር “ግድቡ በተለይም ህዝቡ ለዘመናት አባይ ወንዝ ላይ የነበረውን ቁጭት የሚሽር ነው” ብለዋል።
ከግድቡ ጅማሮ አንስቶም ያለ ልዩነት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የግድቡን ግንባታ እውን ለማድረግ እየተንቀሳቀስ እንደሚገኝ ጠቁመው ባለፉት ስድስት ወራትም ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ገልፀዋል፡፡
“በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ 78 ነጥብ 3 በመቶ ላይ ደርሷል” ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ “በመሆኑም ህዝቡ እያደረገ የሚገኘውን ድጋፍ በማጠናከር የግድቡን ግንባታ ማጠናቀቅ ይገባል” ብለዋል፡፡
የክልሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤትና የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱማሊክ መሀመድ በበኩላቸው በክልሉ ባለፉት 10 አመታት በመደበኛና በተዘጋጁ የተለያዩ ኩነቶች ከ55 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡
ሆኖም ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ከበጀት፣ ከአደረጃጀትና ከሎጅስቲክ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ከመቅረፍ አንፃር ትኩረት እንዳልተሰጠው ጠቁመዋል፡፡
በዋንጫው 5 ወራት የክልሉ ቆይታ 20 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን የጠቆሙት ኃላፊው ከዚህ ውስጥም 12 ሚሊዮን ብር እንደ ክልል በሚከናወኑ የገቢ ማሰባሰብ ተግባራትና 8 ሚሊዮን ብሩ ደግሞ በወረዳዎች ደረጃ የሚሰበሰብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ምስክር ነጋሽ በመድረኩ ላይ ተገኝተው ከንቅናቄው ጋር በተያያዘ የተገኘውን ተሞክሮ አካፍለዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ አመራሮችም እቅዱን ለማሳካት በቁርጠኝነት እንደሚንቀሳቀሱ ያረጋገጡ ሲሆን በእለቱም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ ወይዘሮ ሚስራ አብደላ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫን ለክልሉ ሀኪም ወረዳ አስረክበዋል፡፡