የሰራተኛ ማህበራት የግጭትና አደጋ መከላከል ስትራቴጂ በአፍሪካ በትክክል እንዲተገበር ሊሰሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሰራተኛ ማህበራት የግጭትና አደጋ መከላከል ስትራቴጂ በአፍሪካ በትክክል እንዲተገበር ሊሰሩ ይገባል
አዲስ አበባ ግንቦት 6/2010 በአፍሪካ ያሉ የሰራተኛ ማህበራት የግጭትና አደጋ መከላከል ስትራቴጂ በትክክል እንዲተገበር ሊሰሩ እንደሚገባ የአለም አቀፍ የሰራተኞች ድርጅት ገለፀ። አለም አቀፍ የሰራተኞች ድርጅት ለሶስት ቀናት የሚቆይ ድርጅቱ ግጭትና አደጋን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት የሚያግዝ 'ምክረሃሳብ 205' የተሰኘ መድረክ ለአፍሪካ ቀንድ አገሮች የሰራተኛ ማህበራት የተዘጋጀው አውደ ጥናት ዛሬ ተጀምሯል። በዚሁ ጊዜ የድርጅቱ የሰራተኞች ቢሮ ዳይሬክተር ሚስስ ማሪያ ሄለና እንደተናገሩት፤ በአፍሪካ ሙስና፣ የፍትህ መዛባት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሌሎች ለግጭት መንስኤ እየሆኑ ነው። አንዱ የግጭት መንስኤ የሆነው የስራ አጥነት በስራና ሰራተኛ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር መሆኑን ገልጸዋል። ግጭት የስራ አጥነትን ቁጥር ከመጨመሩም በላይ ለቤተሰብ መለያየትና ለሰውና ንብረት መጥፋት ምክንያተ እንደሚሆን አንስተዋል። የሰራተኛ ማህበራት የግጭት ምክንያቶችን ለመከላከልና በአደጋ የሚከሰት ጉዳትን ከመቀነስ ባለፈ ወደቀድሞ ሁኔታ ለመመለስ አስተዋፅኦ እንዳላቸውም ነው የገለፁት። 'ለአገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ሰላም ወሳኝ እንደሆነ የሰራተኛ ማህበራት ይገነዘባሉ' ያሉት ዳይሬክተሯ በአፍሪካ ያሉ የሰራተኛ ማህበራት ለግጭት አፈታትና አደጋ መከላከል በትክክል እንዲተገበር የበኩላቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል። አውደ ጥናቱ በአገራቸው እያጋጠሟቸው ያሉ ከሰላም እጦትና ስደት ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚረዳቸው ተሳታፊዎች ገልፀዋል። የኢትዮጵያ የሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው 'የአፍሪካ አህጉር ግጭት የሚበዛበት በመሆኑ የስራ አጡና ስደተኛው ቁጥር ከፍተኛ ነው' ብለዋል። የስራ እድል ለመፍጠርና ምቹ የስራ ሁኔታ ለማምጣትም ሰላም መኖር አለበት ያሉት ፕሬዚዳንቱ ለሰላም መረጋገጥ የሰራተኛ ማህበራት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ገልፀዋል። ምቹ የስራ ሁኔታና ሰላም እንዲኖር እንዲሁም ሰራተኛው መብትና ግዴታውን በመለየት ስራውን እንዲያከናውን ማህበሩ ሲሰራ እንደነበር ጠቅሰዋል። 'ምክረ ሀሳቡ የሰራተኛ ማህበራት የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ አቅጣጫ የሚያሳይ በመሆኑ እኛም ለሰራተኛው ምቹ የስራ ሁኔታ ለመፈጠርና ምርታማነቱን ለማሳደግ የምናከናውነውን ተግባር ለመቀጠል ይረዳናል' ብለዋል። በመድረኩ ከኢትዮጵያን፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያና ዛንዚባር የተውጣጡ 30 ተሳታፊዎች ተገኝተዋል። ምክረሃሳብ 205 እ አ አ በሰኔ 2017 የተዘጋጀ ሲሆን በስራ እድል፣ በምቹ የስራ ቦታ ለሰላምና መልሶ ማገገም ያለውን አስተዋፅኦ በተመለከተ የሚመክር መድረክ ነው።