ቀጥታ፡

ፓርቲዎች ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ዝግጅታቸውን ቀጥለዋል

አዲስ አበባ የካቲት 6/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

ፓርቲዎቹ  በነጻናት ለመንቀሳቀስ የገጠሟቸው ችግሮች እንዲፈቱላቸውም ጠይቀዋል።

በዚህ ዓመት ለሚካሄደው አጠቃላይ ምርጫ ቦርዱ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ገልጸዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ ጊዜያዊ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ በቴ ኡርጌሳ አማራጭ ሃሳብ በማምጣት በምርጫው መወዳደር የሚያስችላቸውን ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በሚወዳደሩባቸው አካባቢዎች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የአመራሮች መታሰር፣ የቢሮ መዘጋትና ሌሎች ችግሮች እያጋጠሙን ነው ሲሉም አንስተዋል።

ያም ሆኖ የቦርዱን የጊዜ ሰሌዳ መሰረት በማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ ለመራጩ ሕዝብ አማራጭ ሀሳባቸውን ለማቅረብ አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ገዥው ፓርቲና ምርጫ ቦርድ በተሰጣቸው ኃላፊነት መሰረት ነጻ የመንቀሳቀሻ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ በበኩላቸው ፓርቲያቸው 6ኛው አገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ ያሻግራታል ብሎ ያምናል ብለዋል።

በመሆኑም ፓርቲው ዕጩ በማቅረብ፣ በፖለሲና ሌሎች ለምርጫ ውድድር የሚያስፈልጉ ዝግጅቶችን በማድረግ በሙሉ አቅሙ ለመሳተፍ በጊዜ ሰሌዳው መሰረት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢዜማ ቦርዱ ምርጫ ይካሄድባቸዋል ብሎ በዘረዘራቸው የአገሪቱ ክፍሎች እንደሚወዳደር ጠቁመው፤ "በምርጫ ዘመቻ ወቅት ሁሉም በእኩል የሚስተናገድበት መድረክ ከወዲሁ መፈጠር አለበት" ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ዛዲግ አብርሃ ብልጽግና ፓርቲ ባለው ሃሳብና የድርጅት ጥንካሬ በእኩል ሜዳ በመወዳደር ለማሸነፍ እየሰራ እንደሆነና ውጤቱን የሚወስነው የሕዝብ ድምጽ መሆኑን አንስተዋል።

ፓርቲው ለምርጫ ውድድር እያደረገ ካለው ዝግጅት ጎን ለጎን ምርጫው ፍትሃዊ፣ ሠላማዊና ተዓማኒ ሆኖ እንዲካሄድ በመስራት ላይ መሆኑን ገልጸው፣ ለዚህም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የበኩላቸውን እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ፓርቲዎች የሚያጋጥማቸውን ችግር በተቋቋመው የሦስትዮሽ መድረክ አማካኝነት መፍታት እንደሚችሉም አቶ ዛዲግ አስታውቀዋል።

ብልጽግና ፓርቲ በምርጫው ካሸነፈ መርሃ ግብሩን ተግባራዊ በማድረግ ለአገርና ህዝብ ተጠቃሚነት እንደሚሰራ ገልጸው "ከተሸነፈ በአገሪቱ ተሸንፎ ስልጣን ያስረከበ ፓርቲ ሆነን ማለፍ እንፈልጋለን፤ ለዛም ዝግጁ ነን" ብለዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ ምርጫው በተያዘለት ጊዜ እንዲካሄድ ዝግጅቶች በእቅዱ መሰረት እየተካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ፓርቲዎች ምቹ የመንቀሳቀሻ ሜዳ እንዲኖራቸውና የሚያጋጥማቸውንም ችግር ለመፍታት ከገዥው ፓርቲና ከክልል መስተዳድሮች ጋር በመሆን እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በምርጫ ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታትም ዴስክ ይቋቋማል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አጠቃላይ ምርጫ በግንቦትና ሰኔ 2013 ዓ.ም ለማድረግ እየሰራች ሲሆን ከየካቲት 8 ቀን ጀምሮም የዕጩዎች ምዝገባ እንደሚካሄድ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም