የጋምቤላ መምህራን ትምህርት ና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 2496 ተማሪዎችን አስመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የጋምቤላ መምህራን ትምህርት ና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 2496 ተማሪዎችን አስመረቀ
የካቲት 6 /2013 (ኢዜአ)የጋምቤላ መምህራን ትምህርትና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሠለጠናቸውን ሁለት ሺህ 496 ተማሪዎችን ዛሬ አስመረቀ።
የኮሌጁ ዲን ዶክተር ጋልዋክ ሮን በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት ተማሪዎቹ በመደበኛ፣ ተከታታይና ክረምት መረሐግብር በመምህርነትና ጤና ሙያ ዘርፎች የሰለጠኑ ናቸው።
ከተመራቂዎቹ መካከል 921 ሴቶች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
ኮሌጁ በክልሉ በመካከለኛ ደረጃ ያለውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎት ለማሟላት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።
የዕለቱ የክብር እንግዳ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው በተለይም የትምህርትና የጤና አገልግሎቱን ለገጠሩ ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ ለተያዘው ግብ መሳካት ኮሌጁ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በቀጣይም ኮሌጁ እንደ ክልል ብሎም እንደ ሀገር ጥራት ያለው የትምህርትና ጤና አገለግሎት ተደራሽ ለማድረግ ለተያዘው ግብ መሳከት ጥራቱን የጠበቀ ሥልጠና በመስጠት ብቃት ያለው የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ጠንከሮ እንዲሰራ አሳስበዋል።
ኮሌጁ ለጀመራቸው የሰው ሃብት ልማት ስራዎች መቃናት የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች በኮሌጁ ቆይታቸው ያገኙትን ክህሎት ካላቸው አፍላ ጉልበት ጋር በማቀናጀት ሀገራቸውን በቅንነት እንዲያገለግሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።