መቀሌ ዩኒቨርሲቲ መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራውን ጀመረ

128

መቀሌ ፤ የካቲት 06/2013 (ኢዜአ)  መቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በመቀበል የመማር ማስተማሩን ሥራ መጀመሩን አስታወቀ።

የዩኒቨርሰቲ የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር  ከሰተ ለገሰ  እንደገለጹት  የመማር ማስተማሩን ሥራ የጀመሩት  ከሚጠበቁት 13ሺህ ተማሪዎች ውስጥ  አብዛኛዎቹን    በመቀበል ላይ መሆኑንና የቀሩትንም  እየገቡ ይገኛሉ ብለዋል ።

ተማሪዎቹ  በመቀሌ ማህበረሰብና ተማሪዎች ህብረት አቀባበል እየተደረገላቸው  ከየካቲት 1/2013 ዓ.ም አንስቶ  ትምህርታቸውን መከታተል መጀመራቸውን  አስታውቀዋል።

 የተማሪዎች መማሪያ ክፍሎች ፣መኝታ ቤቶች፣ ምግብ ማብሰያና መመገቢያ አዳራሾችን ከኮሮናን ለመከላከል ታሳቢ ባደረገ  መልኩ ቀድመው መሰናዳታቸውን  ዶክተር ከሰተ አስረድተዋል።

 ከአንደኛ እሰከ ስድስተኛ ዓመት ድረሰ የሚማሩት እነዚህ  ተማሪዎቹ የተቋሙን ህግና  ሥርዓት አክብረው  ትምህርታቸውን መከታታል እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።

ትምህርታቸው መከታተል ከጀመሩት መካከል ከደቡብ ክልል የመጣው የአዲሀቂ ካምፓሰ የሶሾሎጂ ሁለተኛ ዓመት ተማሪ ቸርነት ሽፈራው  ትምህርት በመጀመሩ መደሰቱን ገልጾ በንፁህ መጠጥ ውሃአቅርቦት በኩል  እጥረት ስላለ እንዲስተካከል አስተያየቱን ሰጥቷል።

የእኛ ተማሪዎች ህልም በሠላምና ፍቅር ትምህርታችንን  መከታተልና ተመርቀን  ራሳችንንና ሀገራችን መጥቀም ነው ያለው ደግሞ  የሁለተኛ ዓመት ሶሾሎጂ ተማሪ እንድሪስ  አብዱ ነው።

ከኦሮሚያ ክልል የመጣው ተማሪ ጫላ ሳፋይ በበኩሉ ዩኒቨርሲቲው ለመማር ማስተማር  የሚያስችል የግቢው መሠረተ ልማት  ማሟላቱን ገልጿል።

በምግብ ሠዓት ግን በወረፋ ብዛት ምክንያት ለብዙ ሰዓታት እየጠበቅን መሆኑን ታውቆ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም