የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መጠነኛ የብድር አገልግሎት ማሻሻያ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መጠነኛ የብድር አገልግሎት ማሻሻያ አደረገ

የካቲት 5/2013 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መጠነኛ የብድር አገልግሎት ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቀ።
በብድር አገልግሎት ማሻሻያው ከዚህ ቀደም 8 ነጥብ 63 በአማካይ የነበረው ወደ 10 በመቶ ከፍ መደረጉ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መጠነኛ የብድር አገልግሎት ማሻሻያ ማድረጉን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።
የባንኩን የገቢና ወጪ ልዩነት ለማመጣጠን የብድር ምጣኔ ማሻሻያው ማስፈለጉ ተመላክቷል።
ባንኩ በአማካይ 27 በመቶ የገቢ እድገት ያሳየ ሲሆን 39 በመቶ ደግሞ የወጪ ምጣኔ መመዝገቡን ተገልጿል።
በዚህም በባንኩ የገቢ እና ወጪ ምጣኔ ላይ የ12 በመቶ ልዩነት መኖሩ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ "ከባንኩ የገቢ ምጣኔ ወጪው ብልጫ እያሳየ በመሆኑ የብድር አገልግሎት ማሻሻያ ማድረግ አስፈልጓል" ብለዋል።
ይህን የገቢና ወጪ ምጣኔ ለማመጣጠን ባንኩ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ነው የገለጹት።
በባንኩ ፕሮግራም ላይ 8 ነጥብ 63 በመቶ የብድር ምጣኔ አገልግሎት እንዲሰጥ ቢቀመጥም ከ7 ነጥብ 5 እስከ 11 በመቶ ባለው ውስጥ አገልግሎቱን ሲሰጥ መቆየቱን አስረድተዋል።
በአጠቃላይ የባንኩ የብድርና የውጭ ምንዛሬ አገልግሎት 27 በመቶ በሆነ ገበያ እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ቀሪው 73 በመቶ ደግሞ በዝቅተኛ ወለድ አልያም በነጻ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን አውስተው ይህም በባንኩ የገቢ ምጣኔ እድገት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ መፍጠሩን አስረድተዋል።
የግል ባንኮች ከፍተኛ ብድር እየሰጡ መሆኑ፣ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ማነስና የቁጠባ ባህል አለማደግ ለባንኩ አጠቃላይ የገቢና ወጪ አለመመጣጠን አሉታዊ ጫና መፍጠሩን አብራርተዋል።
ባንኩ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሎ የሚገቡ እንደ ዘይት፣ ስንዴና ስኳር ያሉ ምርቶችም በታሰበው ልክ ለውጥ በማምጣት ገበያውን ማረጋጋት እንዳልቻሉም ተናግረዋል።
በመሆኑም የገቢና ወጪ አለመመጣጠኑን በማስተካከል ከሌሎች ባንኮች ጋር መወዳደር የሚያስችለውን ሁኔታ ለመፍጠር ማሻሻያው አስፈላጊ መሆኑን አቶ አቤ አስረድተዋል።
የማይክሮ ፋይናንስ፣ የመንግስት ቤቶች ግንባታ፣ አትራፊ የንግድ ድርጅቶች፣ የኮርፖሬት ቦንድና የውጭ ምንዛሬ ባንኩ የብድር አገልግሎቶች ማሻሻያ ያደረገባቸው ዘርፎች እንደሆኑም ዘርዝረዋል።
የኮንዶሚኒየም ቤት ቁጠባ መጠን ወደ 3 ቢሊዮን ብር እድገት እያሳየ ሲሆን 53 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለሚገነቡ ቤቶች ብድር መሰጠቱ ተነግሯል።
የብድር ማሻሻያው ከተያዘው የካቲት ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞቹን ቁጥር ከ27 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ማድረሱን መረጃው ያመላክታል።
በሌላ ዜና ባንኩ በበጀት ዓመቱ አጋማሽ ከታክስ በፊት 7 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ትርፍ ሲያስመዘግብ ጠቅላላ ሃብቱ 903 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር መድረሱን ተገልጿል።
42 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት ብዛታቸውን ወደ 1 ሺህ 646 ከፍ ማድረግ ተችሏል፤ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን አዳዲስ ሂቦች በመክፈትም የደንበኞቹን ቁጥር ወደ 27 ነጥብ 5 ሚሊዮን አሳድጓል።
ከውጭ ምንዛሬና ከወጪ ንግድ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሲሰበስብ፤ 47 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችና ለንግድ ተቋማት የሚውል አዲስ የብድር አገልግሎት መስጠቱ ተብራርቷል።
ባንኩ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ለተጎዱ ዜጎች ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉም ተገልጿል።
በግማሽ ዓመቱ በተከናወነ የሃብት ማሰባሰብ 83 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰቡም ተነግሯል።