ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ነጻ ገበያ ተጠቃሚ ለማድረግ የፖሊሲ ማነቆዎች መፈታት አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ነጻ ገበያ ተጠቃሚ ለማድረግ የፖሊሲ ማነቆዎች መፈታት አለባቸው
የካቲት 5/2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ነጻ ገበያ ተጠቃሚ ለማድረግ የፖሊሲ ማነቆዎች መፈታት እንዳለባቸው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አመለከተ።
ምክር ቤቱ 'የኤሌክትሮኒክ ግብይትና የኢትዮጵያ ከባቢ ሁኔታ' በሚል ዛሬ በአዲስ አበባ የፖሊሲ ፓናል አካሄዷል።
የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ እንዳሉት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ነጻ ገበያ ቀጣና ተጠቃሚ ለመሆን ላስቀመጠችው ዕቅድ ስኬትና ፈተናዎችን ለመቋቋም የቴክኖሎጂና የዲጂታል አቅም ሊዳብር ይገባል።
ለንግድ ውድድሩ ማነቆ የሆኑ የፖሊሲና የኤሌክትሮኒክስ ግብይት ችግሮችም በአፋጣኝ ሊፈቱ ይገባል።
በግሉ ዘርፍ ከተሰማሩ ነጋዴዎች አብዛኞቹ ለዓለም አቀፍ ውድድር ብቁ የሚያደርጋቸው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም አቅም እንደሌላቸው ጠቁመው "ይህን ለመቀየር የግሉ ዘርፍ ለአይሲቲና ለዲጂታል ኢኮኖሚ ትኩረት እንዲሰጥ ከመንግስት ጋር መሰራት አለበት" ብለዋል።
ከኤሌክትሮኒክስ ንግድ ባሻገር የመንግስት አገልግሎት በኤሌክትሮኒክስ ሊተሳሰር የሚችልበት ሕጋዊ ስርዓት እንዲዘረጋ የፖሊሲ ማሻሻያ መደረግ እንዳለበትም ነው ወይዘሮ መሰንበት ያመለከቱት።
ምክር ቤቱ ይህንና መሰል ችግሮችን ለመፍታት ስምንት የፖሊሲ ምክረ ሃሳቦችን ለመንግስት ማቅረቡን ጠቁመዋል።
"ችግሩን ለመፍታት በመንግስት በኩል የተጀመሩ ሥራዎች ቢኖሩም አሁንም በፍጥነትና በጥራት መተግበር ያስፈልጋል" ብለዋል።
መድረኩ የንግዱ ማኅበረሰብ በኤሌክትሮኒክስ ግብይትና ዲጂታል ዘርፍ ያሉ ችግሮችና ዕድሎችን በመረዳት ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ለዘርፉ እድገት የበኩሉን ስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማድርግ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የዲጂታል ኢኮኖሚ አማካሪ ወይዘሮ መሪም ሰኢድ አገሪቷን ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ የማሸጋገሩ ሂደት የምርጫ ጉዳይ እንዳልሆነ መንግስት ያምናል ብለዋል።
ይህን ለማሳለጥና በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት በመንግስት በኩል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።
አማካሪዋ "የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በኤሌክትሮኒክስ ለማስተሳሰር የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።
የኃይልና የቴሌኮም ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እንዲሁም አሰራሮችን ለማዘመን ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም አክለዋል።
ኢትዮጵያ ዘመናዊ የንግድ ስርዓት እንዲኖራት ጥራት ያለውና አስተማማኝ የቴሌኮም አገልግሎት ያስፈልጋታል ያሉት ደግሞ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ አብዮት ባየው ናቸው።
በተጨማሪም ተናባቢ የዲጂታል ክፍያ ስርዓትና መተማመንን የሚፈጥሩ የሕግ ማዕቀፎች እንደሚያስፈልጉ ነው የተናገሩት።
ለዚህም መንግስት የግል ዳታ ጥበቃ አዋጅንና ሌሎች የንግድ ስርዓቱን የሚያዘምኑ መመሪያዎች ተግባራዊ በማድረግ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።