ቀጥታ፡

የአሁኑ ትውልድ አባቶቹ በአንድነት በአደዋ የፈጸሙትን ገድል በመጠበቅ ለኢትዮጵያ ብልጽግና ሊሰሩ እንደሚገባ ምሁራን ተናገሩ

ጋምቤላ፤ የካቲት 5/2013 (ኢዜአ) የአሁኑ ትውልድ አባቶቹ በቆራጥነት እና አንድነት በአደዋ የፈጸሙትን የድል ገድል በመጠበቅ ለኢትዮጵያ እደገትና ብልጽግና ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ በጋምቤላ ክልል ምሁራን ተናገሩ።

ምሁራኑ ለኢዜአ እንዳሉት የአደዋን 125ኛ የድል ክብረ በዓል በድምቅት ለማክበር የተጀመርው እንቅስቃሴ ባለፈት 27 ዓመታት በህዝቦች መካከል ልዩነት ለመፍጠር  ሲሰራ የቆየውን የፖለቲካ ሴራ ለማስተካከል የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል።

ከምሁራኑ መካከል ዶክተር ሎው አቡፕ  ፤ የኢትዮጵያ አንድነት መገለጫ፣ የመላው ጥቁር ህዝቦችና የነፃነት ታጋዮች የድል ታሪክ ጭምር አድዋ መሆኑን ገልጸዋል።

’’የጀግኞች አባቶቻችን የአሸናፊነት ሚስጢራቸውም አንድነትና ህብረታቸው ነው ያሉት ምሁራኑ የአሁኑ ትውልድ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ሁሉ ለማለፍ ከአባቶች አኩሪ ታሪክ በመማር ለሀገር እድገት መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል።

ጀግኖች አባቶች የውጭ ወራሪን አሳፍረው የመለሱት በነበራቸው ጠንካራ አንድነትና አይበገሬነት ባህላቸው ነው ያሉት ደግሞ የጋምቤላ መምህራን፣ ትምህርትና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የታሪክ ምሁር አቶ በየነ  ሐመረጥበብ ናቸው ።

ሆኖም  ባለፉት 27 ዓመታት አባቶች  ያቆዩት አብሮነትና  አንድነት  የሚሸረሽር  የልዩነት  የፖለቲካ ሴራ ሲሰበክ መቆየቱንና  ትውልዱም አደዋን ጭምሮ  የሀገሩን  ታሪክ እንዳያውቅ ሲሰራ መቆየቱን አወስተዋል።

ወጣቱ ትውልድ በአባቶቹ የአንድነት መንፈስ ተጋድሎ ከተመዘገበው የአደዋ የድል ታሪክ ተምሮ ሀገሩን ከየትኛውም ወረራ በመጠበቅ እድገቷንና ብልፅግናዋን ለማረጋገጥ  ጠንክሮ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ሳይንስ  ምሁሩ አቶ ሞገስ አበበ በበኩላቸው የአድዋ  ድል ሲታሰብ አይበገሬነትና አንድነትን በተግባር በማሳየት የነጭ የበላይነትን  የሰበር  የኢትዮጵያውን የድል አርማ ነው ብለዋል።

በጀግኖች አባቶች አንድነትና አብሮነት ታፍራና ተከብራ የኖረችውን  ሀገር ለመበተን የህወህት የጁንታ ልዩነቶችን በመስበክ ህዝቡን ለማለያየት ሲሰራ መቆየቱ አስታውሰዋል።

ይህም የተወሰኑ ክፍተቶችን ፈጥሮ ማለፉን ገልጸዋል።

ህወሓት ቢወገድም ጥሎት ያለፈውን የመከፋፋል ሴራ በማክሸፍ ረገድ መንግስታ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የታሪክ ምሁር የሆኑት አቶ ሲሳይ በፍቃዱ ፤ ጀግኖች  አባቶች በአንድነት የውጭ  ወራሪን አሳፍራው የመለሱበት የአደዋ በዓል ተዘንጎቶ ወንድም ወንድሙን የገደለበትን የግንቦት 20 በዓል በህዝቦች መካከል መከፋፈልን በሚፈጥር መልኩ ሲካሄድ መቆየቱን አስታወሰዋል።

የአደዋ የድል በዓልን በድምቀት ከማክበር ባለፈ በሥርዓተ ትምህርቱ ተካቶ ትውልዱ የአባቶቹን የድል ታሪክ እንዲያውቅ ጭምር መሰራት አለበት ብለዋል።

በዓሉን በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች በድምቀት ለማከበር የተጀመረው እንቅስቃሴ ባለፉት ዓመታት በህዝቦች መካከል ልዩነቶችን ለመፍጠር ሲካሄዱ የነበሩ የፖሊቲካ ሴራዎችን አምክኖ የኢትዮጵያን አንድነትን በማጉላት ረገድ የጎላ ፋየዳ   እንደሚኖረው  ምሁራኑ  አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም