ቀጥታ፡

የሴቶችን የፓለቲካ ተሳትፎ ለማጎልበት ቀጣይነት ያለው ሥራ ይጠይቃል

የካቲት 4/2013 (ኢዜአ) የሴቶችን የፓለቲካ ተሳትፎ ለማጎልበት ቀጣይነት ያለው ሥራ ሊኖር እንደሚገባ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመለከቱ።

የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ አስመልክቶ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ተወያይቷል።

የቅንጅቱ የፕሮግራም ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት ዓሊ እንዳሉት የውይይቱ ዓላማ በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ ደረጃና ተሳትፏቸውን ለማሳደግ ፓርቲዎች በሚተገብሯቸው ተግባራት ላይ ለመምከር ነው።

ሴቶች በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ መሳተፋቸው ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሰፊ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ቢሆንም ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር አኳያ ክፍተቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም ቅንጅቱ የሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማጎልበት ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመስራት ማቀዱን አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት ሴቶች በአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ያለምንም ተግዳሮት መሳተፍ የሚችሉበትን ሁኔታ በመፍጠር ረገድ ፓርቲዎች ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል።

በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የሴቶችን ተሳትፎ መፈተሽ የሚገባውም ምርጫ ሲቃረብ ብቻ ሊሆን እንደማይገባም ተጠቁሟል።

ሁሉም ፓርቲዎች ከምርጫ ጊዜያት ባለፈም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማሳደግ ረገድ ተከታታይነት ያለው ስራ መስራት እንዳለባቸውም ተመለክቷል።

ፓርቲዎች ሴቶችን ወደ አመራር ሰጪነት ለማምጣትና ብቃታቸውን ለማሳደግ የተለያዮ ስልጠናዎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ግንዛቤዎችን የማስፋት ስራ እንደሚጠበቅባቸውም በውይይቱ ተጠቁሟል።

የጉዳዩ ባለቤት የሆኑት ሴቶችም የፖለቲካ ፓርቲ አባል ሆነው ለመሳተፍና የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ፍላጎታቸው እምብዛም እንደሆነም ተነስቷል።

በዚህ ሳቢያ ሴቶችን ለማብቃትና የአባላትን ቁጥር ለማሳደግ ችግሮች እያገጠሙ መሆኑንም ነው ፓርቲዎቹ በውይይቱ ወቅት የጠቆሙት።

ሴቶች በተለያዩ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የሚወጡትን ሀላፊነት በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ተሳትፎ በማድረግም እንዲደግሙት በስፋት መስራት እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።

በአገሪቷ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ ከ20 በመቶ እንደማይበልጥ በቅርቡ የወጣ አንድ ጥናት አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም