ቀጥታ፡

ኢትዮጵያና ጅቡቲ የቱሪዝም ፓኬጅ ቀርፀው መዳረሻዎቻቸውን በጋራ ማስጎብኘት ሊጀምሩ ነው

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4/2013 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያና ጅቡቲ የቱሪዝም መስህቦቻቸውን በጋራ የሚያስጎበኙበትና የሚያስተዋውቁበት የቱሪዝም ፓኬጅ ሊያዘጋጁ መሆኑ ተገለጸ።

የቱሪዝም ፓኬጁ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ለመሳብና ከዘርፉ የሚያገኙትን ገቢ ለማሳደግ ያግዛቸዋል ተብሏል።

ለሁለት ቀናት የሚካሄደው የኢትዮ-ጅቡቲ የቱሪዝም የጋራ መድረክ ዛሬ የተጀመረ ሲሆን አገራቱ በቱሪዝም ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት ማጠናከርን ዓላማ ያደረገ ነው።

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ግርማ ኢትዮጵያና ጅቡቲ በኢኮኖሚ፣ በትራንስፖርት፣ በኢነርጂና በንግድ መስኮች ጠንካራ ትብብር እንዳላቸው ገልጸዋል።

ይሁንና በቱሪዝም መስክ ያላቸው የሁለትዮሽ ትብብር እምብዛም እንደሆነና ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን ትብብር የማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ተናግረዋል።

መንግስት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተዳከመውን የቱሪዝም ዘርፍ ለማነቃቃትና የገቢ አማራጩን ለማስፋት ከያዛቸው ዕቅዶች መካከል ከጎረቤት አገራት ጋር ድንበር ተሻጋሪ የቱሪዝም ትስስር ማጠናከር እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ከጎረቤት አገራት ጋር የቱሪዝም መስህቦችን በጋራ በማስተዋወቅ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን መሳብና ለዚህም ከአገራት ጋር የቱሪዝም ምርቶችን ማዘጋጀትና ፓኬጆችን መቅረጽ የዚሁ ዕቅድ አካል ነው ብለዋል።

በዕቅዱ መሰረት ኢትዮጵያና ጅቡቲ ያሏቸውን እምቅ የቱሪዝም ሀብቶች ተጠቅመው መስህቦቻቸውን በጋራ የሚያስተዋውቁበት ሁኔታ የማመቻቸት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ነው አቶ ስለሺ ያስረዱት።

ዛሬ በተጀመረው ፎረም የአገራቱን የቱሪዝም ሀብቶች በተመለከተ ገለጻ መደረጉንና ከጅቡቲ የመጡ የአስጎብኚ ድርጅቶች በአዲስ አበባ የተመረጡ የቱሪዝም መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

የሁለቱ አገራት የአስጎብኚ ድርጅቶችና የአየር መንገዶች የስራ ሃላፊዎች ውይይት በማድረግ  የቱሪዝም ሀብታቸውን በጋራ ማስተዋወቅ የሚያስችላቸውን ፓኬጅ መቅረጽ እንደሚጀምሩም ገልጸዋል።

የቱሪዝም ፓኬጃቸውን ቀረጻ አጠናቀው ጎብኚዎችን የመቀበል ስራ በቅርብ ጊዜ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃልም ብለዋል።

የቱሪዝም ፓኬጁ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች በኢትዮጵያ ማግኘት ያልቻሏቸውን የመዝናኛና የጉብኝት ቦታዎች በጅቡቲ እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑንና ይህም ጎብኚዎችን ለመሳብና ገቢያቸውን ለማሳደግ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

አቶ ስለሺ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፉ የ10 ዓመት ዕቅድ ላይ ድንበር ተሻጋሪ የቱሪዝም ትስስርን ማጠናከር ትኩረት ከሰጠቻቸው ጉዳዮች ዋነኛው ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይ ከኬንያና ታንዛንያ ጋር ተመሳሳይ የቱሪዝም ትስስር የመፍጠር ዕቅድም አላት ብለዋል።

የጅቡቲ የከተማ እቅድ የአየር ንብረትና ቱሪዝም ሚኒስትር መሐመድ አብዱልቃድር ሙሳ የሚዘጋጀው የቱሪዝም ፓኬጅ ሁለቱ አገራት በቱሪዝም ያላቸውን ትብብር ከማጠናከር ባለፈ ቀጠናዊ የቱሪዝም ትብብርን ለማሳደግ ያለው ፋይዳ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ጅቡቲ ከቱሪዝም የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያሏትን ተሞክሮዎች መቅሰም እንደምትሻ ገልጸዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ኢትዮጵያና ጅቡቲ በቱሪዝም ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችላቸው ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ መስህቦች አሏቸው ብለዋል።

አገራቱ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ለመሳብ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶቻቸውን የማሻሻልና አገልግሎቱን የማዘመን ስራ እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ጅቡቲ የቱሪዝም ሀብታቸውን በሚገባ አለማስተዋወቅና የቱሪዝም ምርታቸውን ለመሸጥ የሚያስችል የተቀናጀ የገበያ ስትራቴጂ አለመኖር ከዘርፉ መጠቀም ያለባቸውን ያህል እንዳይጠቀሙ አድርጓል።

ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ለማበጀት ሁለቱ አገራት በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ቱር ኦፕሬተርስ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አንድነት ፈለቀ አገራቱ በጋራ የቱሪዝም ፓኬጅ መቅረጻቸው የቱሪዝም መሰረተ ልማቶችን በጋራ የመጠቀምና ለአስጎብኚ ድርጅቶች በተቀናጀ መልኩ ለማስተዋወቅ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሁለቱ አገራት አስጎብኚ ድርጅቶች የቱሪዝም ምርቶችን በጋራ በማዘጋጀት ያላቸውን ትስስር ማጠናከር እንደሚያስችላቸው አክለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጪ ንግድና የቱሪዝም ማስፋፊያ ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ረጋሳ ከፍአለ የቱሪዝም ፎረሙ ኢትዮጵያ ቱሪዝምን ጨምሮ በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እየሰራች ያለችው ስራ አካል እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ጅቡቲ በቱሪዝም ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ማሳዳግ ከቻሉ የአገራቱን የሁለትዮሽ የኢኮኖሚ ትስስር ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያና የጅቡቲ አስጎብኚ ድርጅቶች ነገ የጋራ የቢዝነስ ውይይት ያካሂዳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም