ጀግኖች አባቶች በአንድነት በአድዋ ከተቀዳጁት ድል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊማር ይገባል... ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ጀግኖች አባቶች በአንድነት በአድዋ ከተቀዳጁት ድል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊማር ይገባል... ምሁራን
ሠመራ፤ የካቲት 4/2013(ኢዜአ) ጀግኖች አባቶች ልዩነታቸውን አቻችለው ለሀገር ክብርና ነፃነት በአንድነት በመቆም በአድዋ ከተቀዳጁት ድል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊማር እንደሚገባ የሠመራ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ሥነ-ዜጋ ምሁራን ተናገሩ።
ከምሁራኑ መካከል አቶ አብዱልመጂድ ጢቻ ለኢዜአ እንዳሉት "ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ከሁሉም የሀገሪቱ ጫፍ በአንድነት በመነሳት ለሃገራቸው ነፃነት ፣ክብርና ሉአላዊነት መከበር በአድዋ ታላቅ ታሪካዊ ድል ተቀዳጅተዋል።"
ድሉ በተለይም ቀኝ ገዢዎች አፍሪካን ለመቀራመት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በመሆኑ በአሰከፊ ጭቆና ቀንበር ስር የነበሩ ጥቁር ህዝቦች እራሳቸውን ነፃ ማውጣት እንደሚችሉ መነቃቃት የፈጠረ ነው ብለዋል።
ከዚህ አኩሪ ድል ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ያለምንም የብሄርና እምነት እንዲሁም አመለካከት ልዩነት ሀገርን ማስቀደም እንደሚኖርበት መማር አለበት ነው ያሉት።
"አሁን ሀገራችን ከህዳሴው ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ የውስጥና ውጭ ጠላቶቻችን ሊበትኑን በሚንቀሳቀሱበት በዚህ ወቅት ይህ ትውልድ ቅራኔውንም ሆነ ልዩነቱን አቻችሎ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነቱን አጠናክሮ ለሀገሩ ዘብ በመቆም እንደ ጀግኖች አባቶቹ ታሪክ ሊሠራ ይገባል" ብለዋል።
ሌላው የዩኒቨርስቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ምሁር አቶ ኡርጌሳ አለሙ "የአድዋ ድል መቼም ሊደበዝዝ የማይችል ደማቅ የነጻነት ተጋድሎ ብሎም ነጮች በጥቁሮች ላይ የነበራቸውን የበላይነትን የቀየረ ነው" ሲሉ ገልጸዋል።
እንግሊዝና ፈረንሳይን ጨምሮ በወቅቱ ሃያላን ለሚባሉ ሀገራት ኢትዮጵያ ነጻና ሉአላዊት ሀገር መሆኗን ያሳየችበትና ተጨማሪ አለም-አቀፍ ክብር የተጎናጸፈችበት ድል ነው ብለዋል።
ይህ የሆነው ሁሉም ኢትዮጵያውያን "እምቢ ለሃገሬ" ብለው በፍጹም ሀገር ወዳድነት ጥልቅ መንፈስ ከጫፍጫፍ በአንድነትና ጀግንነት በመተባበራቸው እንደሆነ አስረድተዋል።
ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን በነፃነት መኖር የሚቻለው ሀገር ታፍራና ተከብራ ስትቆይ መሆኑን በማመን ልዩነታቸውን አቻችለው አድዋ ላይ ከተቀዳጁት ድል ሁሉም ዜጋ ሊማር እንደሚገባ ነው የተናገሩት።
"ታሪኩን የማያውቅ ሰውም ሆነ ትውልድ መነሻና መድረሻውን እንደማያውቅ ተጓዥ ነው" ያሉት ምሁሩ ትውልዱ ይህን የአባቶቹን አኩሪ ታሪክ በማወቅ የብሔር፣ እምነትና አመለካከት ልዩነት ቀድሞም የነበረ ወደፊትም የሚኖር እውነት መሆኑን ሊገነዘብ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
"ልዩነት በጋራ ሀገራችን ጉዳይ በአንድነት ከመቆም እንደማይገድቡን ከጀግኖች አባቶቻችን ድል ምስጢር ተምረን በጋራ በመቆም ወቅታዊ ችግሮችንም በውይይት እየፈታን አንድነታችንን የበለጠ ማጠናከር አለብን" ብለዋል።
"ተደማሪ ታሪክ ለመስራትና ድሎች ለማስመዝገብ ልንጠቀምበት ይገባል" ሲሉም አቶ ኡርጌሳ አብራርተዋል።
የአድዋ ድል ሀገር የማዳንን ጥሪ ተቀብለው በየትኛውም ጫፍ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን የተሳተፉበት የሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አኩሪ ድል መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው የዩኒቨርሲቲወ የሥነ- ዜጋና ሥነ-ምግባር መምህር አቶ እስጢፋኖስ ባለው ናቸው።
ትውልዱ ከአድዋ ጀግኖች ድል መደማማጥንና መተባበርን እንዲሁም ጥልቅ የሀገር ፍቅርን በመውሰድ ለወቅታዊ ሀገራዊ የአብሮነትና አንድነት ፈተናዎች በአሸናፊነት ለመወጣት ትምህርት ሊወሰድበት ይገባል ብለዋል።
በተለይም ልዩነቶችን አለአግባብ በማጉላት አሁን የተፈጠረው የመገፋፋትና ጥላቻ አካሄድ በማቆም ሀገራዊ አንድነትና አብሮነት ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የአድዋ ድል የአንድነትና አብሮነት ጠንቅ የሆኑ መጠላላትና ከመጠን ያለፈ መገፋፋቶችን ለማከም የሚያስተምር ገድል መሆኑንም አስረድተዋል።