አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ይሰራል - ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ይሰራል - ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 4/2013 ( ኢዜአ) አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እንደሚሰራ የከተማዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
በክቡር ዶክተር አበበች ጎበና ስም የተሰየመው የእናቶችና ህጻናት ሆስፒታል ዛሬ ተመርቋል።
በምርቃት ስነ- ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንዳሉት በከተማው ለነዋሪዎቹ በቂ የሆነ የህክምና አገልግሎት መስጫ ተቋም የለም።
በተለይ ለእናቶችና ህጻናት በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩ ብዙ እናቶች ለእንግልትና ለሞት ይዳረጋሉ።
ይህንንና ሌሎች የጤና አገልግሎቶችን በማሻሻል ከተማውን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ አስተዳደሩ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
አስተዳደሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ለህክምና ወደ ውጭ ሄደው የሚያወጡትን ጊዜና ገንዘብ ለማስቀረትም እየሰራ ነው ብለዋል ምክትል ከንቲባዋ።
ዛሬ ለአገልግሎት ክፍት የሆነው ሆስፒታልም አስተዳደሩ ለጤናው ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ማሳያ ነው ብለዋል።
ሆስፒታሉ በ700 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባ ሲሆን በውስጡ ከ400 በላይ አልጋዎች አሉት።
በአንድ ጊዜ ሰባት እናቶችን በቀዶ ህክምና ማዋለድ እንደሚያስችልም ወይዘሮ አዳነች ተናግረዋል።
ሆስፒታሉ በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ከወረቀት ነጻ የሆነ አገልግሎት ስለሚሰጥ የእናቶችና የህጻናትን እንግልት ይቀንሳል ብለዋል።
በ22 ሺህ ካሬ መሬት ላይ ያረፈው ሆስፒታል በአገሪቱ ከ60 ዓመታት በኋላ የተገነባ የእናቶችና ህጻናት ሆስፒታል ነው።
ለአራት ዓመታት ያለ አገልግሎት የተቀመጠው የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ነው ወደ ሆስፒታልነት የተቀየረው።
በከተማው ያለ አገልግሎት የተቀመጡ ቦታዎችና ህንጻዎችን ወደ ልማት መቀየር እንደሚቀጥል ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል።
ሆስፒታሉ ከሌሎች የተለየና እውቀትና ሃብት ሳይኖራቸው ለብዙ ህጻናት እናት በሆኑት በክቡር ዶክተር አበበች ጎበና መሰየሙ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ በበኩላቸው በአገሪቱ የእናቶችና ህጻናትን ሞት በመቀነስ ረገድ አበረታች ውጤቶች ቢኖሩም ከተደራሽነትና ከጥራት አንጻር ቀጣይ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል።
ሆስፒታሉ የእናቶችና ህጻናት ጤና አገልግሎትን በእጥፍ እንደሚያሳድግም አስታውቀዋል።
በተጨማሪ የልህቀት ማዕከል በመሆንም ከሌሎች ተቋማት ለሚመጡ የጤና ባለሙያዎች የእውቀትና የክህሎት ማሰልጠኛ ይሆናል ነው ያሉት።
የምርቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ ክብርት ዶክተር አበበች ጎበና፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መዓዛ አሸናፊ፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ፣ የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ታዋቂ ግለሰቦችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።