ቀጥታ፡

ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በብቃት ሲመሩ የነበሩት ኢንጂነር ስመኘው በቀለ ሞተው ተገኙ

አዲስ አበባ ሀምሌ 19/2010 የአገር ኩራት የሆነውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በብቃት ሲመሩ የነበሩ ኢንጂነር ስመኘው በቀለ መስቀል አደባባይ መኪናቸው ውስጥ ሞተው ተገኙ። ዛሬ ማለዳው ላይ መስቀል አደባባይ መሃሉ ላይ የቆመ ወርቃማ ቀለም ያለው ኮድ 3 አ.አ 29722  መኪና ውስጥ  ነው ኢንጂነሩ ብቻቸውን ተዘግቶባቸው መኪና ውስጥ ሞተው የተገኙት። መኪናው ፖሊስ ተጠግቶት ምርመራ እስከሚጀምር ድረስ ሞተሩ እንዳልጠፋና መኪናውም ተቆልፎ ወይም /ስኩሬስ/ ተደርጎ እንደነበር መታዘብ ችለናል። ፖሊስም በስፍራው እንደደረሰ መኪናውና አካባቢው ላይ ያለውን የአሻራ ናሙናዎችን ሲሰበስብም ተመልክተናል። በስፍራው ያለው ምርመራ ከተጠናቀቀም በኋላ አስክሬኑ ለምርመራ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተወስዷል። የሞታቸውን መንስኤ ለማጣራት የፖሊስ አባላት ምርመራ እያካሄዱ ሲሆን በሆስፒታሉ ምርመራ ተደርጎላቸው የሚደርሰውን ውጤት ፖሊስ ከሰዓት በኋላ መግለጫ እንደሚሰጥም ይጠበቃል። ኢንጂነር ስመኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ቀን ጀምሮ በዋና ስራ አስኪያጅነት ሲመሩ የነበሩ ሲሆን ከዚያም በፊት ታላላቅ ግድቦችን በበላይነት የመምራት ሃላፊነትን በብቃት የተወጡ የአገር ባለውለታ መሆናቸውን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም