የህዳሴ ግድብ የአፍሪካ ትንሳኤ ምልክት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ የአፍሪካ ትንሳኤ ምልክት ነው
የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ አሜን ጋሻው ስለህዳሴ ግድብና የአባይ ውሃን አስመልክቶ ሃርቫርድ ኢንተርናሽናል ሪቪው ድረገጽ ላይ ባስነበበችው ትንታኔ ከውጭ ሆኖ ለሚመለከት የአባይ ወንዝ ውሃ እንደማንኛውም አይነት ወራጅ ውሃ ነው። ወንዙን ተጎራብተው ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ግን ለየት ያለ ትርጉም አለው ትላለች። ኢትዮጵያውያን የወንዙ ፏፏቴ ለአይናቸው ማረፊያ ውሃውን መረብ ጥለው አሳ የሚያሰግሩበት፣ ልብሳቸውን የሚያጥቡበት፣ የዜግነት ክብር መግለጫቸው፤ በአጠቃላይ ከነፍስያቸው ጋር ቀጥተኛ ትስስር አለው በማለት የቦስተን ዩቨርሲቲው ፕሮፌሰር ጄምስ ማካን የተባሉት ከቦስተን ዩኒቨርሲቲ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ መግለጻቸውን ዋቢ አድረጋለች።
ኢትዮጵያ በርካታ ሚሊዮን ዜጎቿን የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ለማደረግና አንዱ ከድህነት መንገድ አድርጋ በማሰብ እያስገነባችው ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የግብጽን ብቸኛ የወንዙ ተጠቃሚነት የሚያስቀር ሲሆን ይሄ አይነቱ የኢትዮጵያ የልማት ፍላጎት ግብጽን ሊያስደስታት አለመቻሉ ይገለጻል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአባይ ውሃ በዓለም አቀፍ ጥላቻ እንዲመረዝ ጥረት ግብጽ እያደረገች ስለመሆኑ የምትገልጸው ተመራማሪዋ በርካታ ትንቅንቆች ያሉበት ይሄ አይነቱ የኢትዮጵያ የልማት እንቅስቃሴ አብዛኛው ህዝብ ልብ ባይለውም ለበርካታ ጊዜያት ጥረት ሲደረግ እንደቆየ አስታወሳለች።
ግንባታው ከመጀመሩ ከግማሽ ምዕተ ዓመት ገደማ በፊት ኢትዮጵያ ከዩናይትድ ስቴትስ ሬክላሜሽን ቢሮ ጋር በመተባበር በአባይ ወንዝ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የአዋጭነት ጥናት ያካሄደች ሲሆን በቀጣዮቹ በርካታ ዓመታት በእርስበርስ ጦርነት፣ በህዝባዊ አብዮትና በሌሎች የውስጥ ጉዳዮቿ ባተሌ የነበረችው ኢትዮጵያ ወንዙ ላይ የልማት ፕሮጀክቱቶችን ለመተግበር ባለመቻሏና የአባይ ውሃ አጠቃቀምን በሚመለከት ከግብፅ ጋር የተደረጉ ንግግሮች ሁሉ በግብጽ ግትርነት ምክንያት ይሄ ነው የሚባል ውጤት ሳያመጡ ያለስምምነት ቀርተዋል ነው ያለችው።
በዚሀ ግትርነት ውስጥ ያለችው ግብጽ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት በማድረግ ለመወያየት የተደረጉ ጥረቶችን ዋጋ በማሳጣትና አላስፈላጊ ንትርክ እየፈጠረች ዛሬ ላይ ብትደርስም ግብጽ በጉዳዩ እስክትስማማ ተብሎ ኢትዮጵያ የገነባችውን ግድብ ውሃ አትሞላም ማለት አይቻልም የምትለው ተመራማሪዋ ለአስር አመታት ያህል በረቀቀ መንገድ የኢትዮጵያ ህልም እንዳይሳካ የሚሰሩ አለማቀፍና የሃገር ውስጥ አካላት አፍራሸና ጎታች እንቅስቃሴዎችን በብልሃት በማለፍ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ እንደተቃረበ መሆኑን ገልጻለች።
“የስፔኑ ኤል ግሪኮ እጅግ ከፍተኛ ጥበባዊ ችሎታ ቢኖረው ፣የፍቅር ታሪኩ ቢመስጥም ፣ሃገሩን ከእዳና ከግጭቶች አረንቋ መንጭቆ ቢያወጣም የመጨረሻ አሟሟቱ በድህነትና ምስጋና በማጣት” እንደነበር ያስታወሰችው ተመራማሪዋ፤ ኤል ግሪኮ ለሃገሩ ያደረገውን አስተዋጽኦ አስታውሶ የስፔን ትንሳኤ ፈር ቀዳጅ የሚል ስያሜ ለመስጠት ስፔናውያን አራት መቶ አመታት እንደጠበቁት ሁሉ ኢትዮጵያም ሰማኒያ አምስት በመቶ ውሃው የእሷ ሆኖ እያለ ለግብጽና ሱዳን ያደረገችው ውለታ ቦታ አልተሰጠውም ብላለች።
ኢትዮጵያ ግድቡን ለመገንባት የደረሰችበት ውሳኔ እጅግ የዘገየ ከመሆኑ አንፃር ለረጅም ጊዜ የተከማቸና ትልቅ በመሆኑ ፕሮጀክቱን ህዳሴ ሊያስብለው የቻለ እንደሆነም ገልጻለች። ለአመታት ኢትዮጵያ ላይ ሲደርስ የቆየው የአካባቢያዊና ፖለቲካዊ መገፋትና አድልዎ፣ የባህር በር ማጣቷና ያላትን እምቅ ሃብት እንዳትጠቀም ያደረጋት ሲሆን ከአጠቃላይ ህዝቧ ከሰላሳ በመቶ በታች የሚሆነው ብቻ በአነስተኛ ደረጃ የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያገኝና ከግማሽ በላይ የሚሆነው ደግሞ ምግቡን የሚያበስለው እንጨት መሆኑን ተመራማሪዋ አውስታለች።
ይህ ክስተት ኢትዮጵያ ኃይል የማምረት አቅም እንደሌላት ማሳያ ባይሆንም ያላትን እምቅ የንፋስ ፣የፀሐይ እና የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ሃይል ለመጠቀም የሚያስችል መሰረተ ልማት ባለመኖሩ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት እና እሱን አልምቶ ለራሱ በመጠቀም፣ ለሌሎችም ሊተርፍ የሚችለው ሕዝብ በድህነት እንዲኖር የተፈረደበት ሲሆን በርካቶቹ የኢትዮጵያ ገጠሮችና አነስተኛ ከተሞች እስካሁን የኤሌክትሪክ ሃይል አላገኙም።
እንደ ተመራማሪዋ ገለጻ የህዳሴ ግድብ ከድህነት ለመውጣት ጥረት እያደረገች ላለችው ኢትዮጵያ የሀይል እጥረቱን ለመፍታት ከተቀመጡት መፍትሄዎች መካከል አንዱና ወነኛው ሲሆን ግብጽ ከበርካታ አመታት በፊት በገነባችው የአስዋን ግድብ 45 በመቶውን የኃይል ፍላጎት በማሟላት ደለልን በመከላከል፤ ለመስኖ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝና ለሃገሪቱ ጥቅል አመታዊ ምርትም አራት በመቶ ቀጥተኛ ድርሻ ያለው እንደሆነም ጠቅሳለች።
ከሌሎች ሃገራት የእድገት ደረጃ አኳያ የኢትዮጵያ እድገት በእጅጉ ወደ ኋላ የቀረ በመሆኑ የህዝቦቿን ህይወት ለውጣ ከሌሎቹ ሃገራት ጎን ለመሰለፍ ሁሉን አቀፍ የእድገትና የልማት እቅዶችን እውን ለማድረግ የህዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ ጥያቄ ውስጥ እንደማይገባ ያብራራችው ተመራማሪዋ፤ በየአመቱ ከአስር በመቶ በላይ ምጣኔ ሃብታዊ እድገት በምታሳየው ኢትዮጵያ ያለው ስር የሰደደ የሃይል እጥረት በግድቡ መጠናቀቅ ሙሉ ለሙሉ ባይፈታም በእጅጉ ሊቃለል ይችላል ብላለች።
ጣሊያናውያን ዘመነ ህዳሴ ሲሉ በሚጠሩት 15ኛው መቶ ክፍለዘመን አለመረጋጋት፣ ግድያና አመጽ የነገሰባትን ፍሎረንስ ከተማን በሚያማምሩ የባህል፣ የኤኮኖሚ እንዲሁም የፖለቲካ ማእከላትና በሌሎች ህንጻዎች ያስዋባት ኮስሞ ዲ ሜዲቺ የተባለው የኪነህንጻና የከተማ ልማት ባለሙያ፤ ከተማዋ ላይ የእጅ አሻራዎቹን ሲያስቀምጥ አብረውት የከተማዋ ነዋሪዎችም ተሳታፊ እንደነበሩ ያስታወሰችው ተመራማሪዋ፤ ከአለም ማህበረሰብ የተቃውሞ ጩኸት በተቃራኒው ሁሉም ኢትዮጵያውያን ላለባቸው የሃይል ረሃብ ማስታገሻ እንዲሆን ለግድቡ የቻሉትን በማደረግ ግንባታውን እዚሀ እንዳደረሱት ገልጻለች።
ሃገራት ብሄራዊ ችግር በገጠማቸው ጊዜ ሁሉ ቦንዶችን አዘጋጅተው እንደሸጡ፣ የአለም ጦርነቶችን የኢኮኖሚ ድቀቶችን እንዲሁም ድርቆችን ያስታወሰችው ተመራማሪዋ፤ የኢትዮጵያ መንግስት አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣውን የቦንድ ሽያጭ ከብሄራዊ ክብርና አርበኝነት ጋር በማያያዝ ገንዘብ ለማሰባሰብና ቀሪውን ገንዘብ ከሃገር ውስጥ ምንጮች፣ ከሌሎች የልማት አጋሮችና ከግብጽ በተቃራኒ ከቆሙ የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ለማግኘት የሄደበት ርቀት የሚደነቅ መሆኑንም አንስታለች።
እ.ኤ.አ በ1996 ኢትዮጵያ በአለም ባንክና በአለም የገንዘብ ድርጅት የቀረበላትን የመዋቅር ማስተካከያ መርሃግብር ተግባራዊ አድርጋ አየር መንገድን ጨምሮ ሁሉንም የመንግስት የልማት ድርጅቶች በአጭር ጊዜ ወደ ግል ማዞር ባለመፈለጓ ዳግመኛ የገንዘብ ድጋፍ ጥያቄ እንዳታቀርብ ማእቀብ ተጥሎባት እንደነበር በማስታወስ ያለ ማንም እገዛ ግድቡን በኢትዮጵያውያን አቅም እንዲገነባ በማደረግ ራሷን ከብድር ጥያቄና አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት መከላከል ችላለች።
በልእለ ሃያሏ አሜሪካ የሚዘወሩት እነዚህ ድርጅቶች ለድሃ ሃገራት የልማት ጥያቄዎች እገዛ ከማድረግ ይልቅ ነገሮችን ማወሳሰበና ተስፋ ማስቆረጥ ላይ በርተትው እየሰሩ መሆኑን ያብራራችው የመራማሪዋ፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በውስጥ የሚፈጠሩ ግጭቶች ቢኖሩም የግድቡ ግንባታ መጀመር ለአንድ ሃገርና ለአንድ አላማ አሰባሳቢ ምክንያት ሊሆን በቅቷል ብላለች።
ተመራማሪዋ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም በሚፈጠር ምዝበራና የገንዘበ ብክነት ሃምሳ የሚሆኑ ሰዎች ላይ ክስ የመሰረተው የኢትዮጵያ ጠቅላይ አቃቤህግ ትኩረቱን ግድቡን ሲመራ በነበረው ሜቴክ ላይ ስለማድረጉ አስታውሳ ለግድቡ ግንባታ መዘግየትና ደካማ የስራ አፈጻጸም ፣ ለግድቡ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ስመኘው በቀለ ግድያና ተያያዥ ጉዳዮች ዋነኛ ተጠያቂው ሜቴክ ስለመሆኑ የአቃቤ ህግ ማስረጃዎችን አጣቅሳ ትሞግታለች።
በሃገረ አሜሪካ የሃርለም ህዳሴ ሲነሳ ስሟ ቀዳሚ ሆኖ የሚጠቀስላት ሞገደኛዋ ጸሃፊ ጥቁር አሜሪካዊት ዞራ ኒል ሃርስቶን የሃርለም ህዳሴንና የአፍሪካ አሜሪካውያንን የአኗኗር ሁኔታ በሚመለክት የምትታዘበውንና የሚሰማትን ያለምንም ይሉኝታ በመጻፍ እወቁት ስትል ብትኖርም እስከ እለተ ሞቷ ድረስ በስነጽሁፍ ማህበረሰቡ ውስጥ እዚህ ግባ የሚባል ቦታ ሳይሰጣት የተቀበረችበት ቦታም ሳይታወቅ እንደቀረ ያነሳችው ተመራማሪዋ፤ ታላቁ የህዳሴ ግድብም ሃያላኑ ያስቀመጡትን እንቅፋት በጥበብ በማለፍ እዚህ እንደደረሰ ገልጻለች።
እንደ ተመራማሪዋ ገለጻ ከግብጽ ጋር በግዙፍ የግብርና ኢንቨስትመንት የተሳሰረችው እስራኤል ፣የግብጽ የረጅም ጊዜ የስትራቴጂ አጋር አሜሪካ እንዲሁም ኮንጎና ሱዳንን የመሳሰሉት ከሰሃራ በታች ያሉ ሃገራት ባለባቸው የጥቅም ግጭቶች የተነሳ የግድቡ ተገንብቶ መጠናቀቅ ቢቃወሙት እንደማይገርምና ሃገራት ሁሉ እንቅስቃሴያቸው ጥቅምና ኪሳራቸውን ያሰላ በመሆኑ የሃገራት ሁለንተናዊ አቅም እያደገ ሲመጣ ማን ከማን ጋር ሆነ የሚለው ጉዳይ ያነ ያህል አሳሳቢ አይሆንም ብላለች።
አሜሪካ የግድቡን ውሃ አሞላል በሚመለከት ኢትዮጵያን፣ ሱዳንና ግብጽን ለማደራደር በወሰደችው ሚና ውስጥ ይፋዊ ውግንናዋን ለግብጽ አድርጋ ለኢትዮጵያ ልትሰጠው ያሰበችውን አንድ መቶ ሰላሳ ሚሊየን ዶላር መከልከሏ ገለልተኝነቷን ጥያቄ ውስጥ የሚከተው ሲሆን፤ ሶስቱ ሀገራት ያለማንም ጣልቃ ገብነት የሚያደርጓቸውን የሶስትዮሽ ውይይቶችና ድርድሮች ያለውጤት እንዲጠናቀቁ በማድረግ በአፍሪካ ሃገራት መካከል የጥርጣሬ ዘር የመበተን እድሉ ሰፊ ነው።
እ.ኤ.አ. በ2008 በዓለም ባንክ አደራዳሪነት የተደረገው ስምምነት ኢትዮጵያ የምትገነባው የትኛውም ግድብ የ95 በመቶ የግብጽ ዜጎችን የውሃ ድርሻ ይጎዳል በሚል መጠቀሱ ግብጽ ኢትዮጵያ ከድታኛለች የሚል ስሜት እንድትይዝና 66 በመቶ የነበረውን የግብጽ የውሃ ድርሻ ወደ 90 በመቶ እንድታሳድግላት ደጋግማ ጥያቄ ስታቀርብ ብትቆይም አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የግድቡን መጠን መቀነስም ሆነ የታሰበውን ውሃ እንዳይሞላ በማድረግ ግድቡን ካለው አቅም በታች ማሰራት የማይታሰብ ነው።
ተመራማሪዋ ሱዳንም በተደጋጋሚ ለመንግስታቱ ድርጅት የላከቻቸው የተማጽኖ ደብዳቤዎች ከግብጽ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸውና የግድቡ የውሃ ሙሌት የበርካታ ሚሊዮን ሱዳናውያን አርሶአደሮችንን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥልና የሮዛሪ ግድብ ደህንንትን የሚጎዳ ስለመሆኑ የሚገልጽ ሲሆን ግድቡንና የውሃ ሙሌቱን በሚመለከት ዴሞክራቲክ ኮንጎ የምታራምዳቸው ለግብጽ የወገኑ ሃሳቦች የወደፊት የኢትዮጵያ የውሃና የተፋሰስ ልማት ትልሞች ላይ አፍራሽ አሻራ ትተው የማለፍ እድላቸው ሰፊ እንደሆነ ገልጻለች።
ተመራማሪዋ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ሃይል ከማመንጨት ባሻገር በአፍሪካ አህጉር የነበረውን የፖለቲካና የሃይል አሰላለፍ ከስሩ በመቀየር የተዛባውን የሃገራት ግንኙነት እንደሚያሻሽልና የኢትዮጵያንም የመደራደር አቅም በመጨመር በአካባቢው ላይ ያላትን ተጽእኖ ፈጣሪነት እንደሚያሳድግ ተስፋ ተጥሎበታል ብላለች።
ግድቡን የመሙላቱ እና የድርድሩ ሂደቶች አንዴ ከተጠናቀቁ፣ ግድቡ ከሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል በተጨማሪ በሰከንድ ከ19ሺህ ኪዩቢክ ሜትር በላይ የሚሆን ጎርፍ የማቃለል አቅም ያለውና ተጨማሪ ግማሽ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ እንዲለማ እድል የሚሰጥ መሆኑም ተጠቅሷል።
ወደ ሱዳን የሚሄደውን አፈር በማስቆም በሱዳን የሚከሰተውን የጎርፍ መጥለቅለቅ በመቀነስ ግድቡ ከተሰራበት ቴክኖሎጂ አኳያ በአመት በትነት የሚባክነውን ስድስት ቢሊየን ኩቢክ ሜትር ውሃ ለመያዝ ያስችላል። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተለይ ለኢትዮጵያ እንዲሁም በአጠቃላይ ለአፍሪካ ልማትና ለውጥ ከሚኖረው አስተዋጽኦ አንጻር የአፍሪካ ህዳሴ ምልክት ቢባል እንደማይበዛበት የገለጸችው ተመራማሪዋ የአፍሪካ ሃገራት ልዩነቶቻቸውን አቻችለው ለጋራ ጥቅማቸው በጋራ መስራት እንዲችሉ የግድቡ ግንባታ መጀመር ጉልህ አንድምታ አለው በማለት ጽፋለች።