በትግራይ ክልል 92 የምግብ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የአስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ እየቀረበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል 92 የምግብ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የአስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ እየቀረበ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 4/2013 ( ኢዜአ) በትግራይ ክልል በ36 ወረዳዎች በሚገኙ 92 የምግብ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የአስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ ስርጭት እየተካሄደ መሆኑን የሠላም ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከ 26 በላይ ከሚሆኑ ዓለም አቀፍ እና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች አፋጣኝ የምግብ ስርጭት የማድረስ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም አመልክቷል፡፡
70 በመቶው የምግብ አቅርቦት በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ ሲሆን ቀሪው 30% በልማት አጋሮች እና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የተሸፈነ እንደሆነ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
እስካሁን ድረስም በክልሉ 2 ሚሊዮን 7 ሺህ ወገኖቻችንን ተጠቃሚ ናቸው ያለው መግለጫው ፣ለህፃናት፣ እናቶችና አረጋውያን የአልሚ ምግብ አቅርቦትን የበለጠ ለማስፋትና ምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶችን በተፈለገው መጠን ለማቅረብ ከአጋር አካላት ጋር በቅርበት እየተሠራ መሆኑም ተመልክቷል።
በቀጣይም የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችም ስርጭት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስታወቀው የሠላም ሚኒስቴር ፣በሁሉም የክልሉ ማዕዘን ለሚገኙ የምግብ አቅርቦት ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ለመድረስ ያልተቆጠበ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጿል፡፡