የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ የሰጠው መግለጫ ሚዛናዊነት የጎደለው ነው.... ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ የሰጠው መግለጫ ሚዛናዊነት የጎደለው ነው.... ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን
የካቲት 3/2013(ኢዜአ) የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ የሰጠው መግለጫዎች ሚዛናዊነት የጎደለው መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የአውሮፓ ህብረት መልዕክተኛ ፔካ ሃቪስቶን ዛሬ በቢሮአቸው አነጋግረዋል፡፡
በትግራይ ክልል ከጊዜያዊ አስተዳደርና ከአለም አቀፍ ሰብአዊ ድጋፍ ሰጭ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሰብአዊ ዕርዳታ እየተሰራጨ መሆኑንና በአሁኑ ጊዜ 26 የሚሆኑ የአለም አቀፍ ዕርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ከመንግስት ፈቃድ ተሰጥቷቸው ዕርዳታውን ለማዳረስ እየሰሩ እንደሚገኙ አቶ ደመቀ ለመዕክተኛዉ ገልጿል፡፡
እንደዚሁም በህወሃት የጥፋት ቡድን ጥቃት የደረሰባቸውን መሰረተ ልማቶችን የመጠገን ሥራ እንደቀጠለም አብራርተዋል፡ይሁንና የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ የሰጠው መግለጫዎች ሚዛናዊነት የጎደለው መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ፤ በህብረቱ የሚደረጉ ድጋፎችን ለማዘግየት የሚደረጉ ጥረቶች የኢትዮጵያን መንግስት የሚያሳዝን ነው ብለዋል፡፡
ህብረቱ የኢትዮጵያ ስትራቴጅካዊ አጋርነቱን አጠናክሮ በክልሉ ያለውን የሰብአዊ ዕርዳታ ድጋፍ እና በአገሪቱ እየተካሄደ ያለውን የለውጥ ሥራ እንዲደግፍም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከሱዳን ጋር የተፈጠረውን የድንበር ችግር በስፋት በማብራራት ፤ የሱዳን ወገን ከግጭቱ በፊት ወደ ነበረበት ቦታ ተመልሶ፤ ለችግሩ ቀደም ሲል በሁለቱ አገሮች መካከል ባሉ ስምምነቶች መሰረት ሰላማዊና ዘላቂ መፍትሔ እንዲገኝ የኢትዮጵያ አቋም መሆኑን አስረድተዋል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሽ በቀለ በበኩላቸው በህዳሴ ግድብ ዙሪያ እየተደረገ ያለውን ድርድር በማስረዳት ፤ የአፍሪካ ችግር በአፍሪካውያን በሚለው መርህ መሠረት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት እንድደረስ የኢትዮጵያ ፍላጎት መሆኑን ለመልዕከተኛው አስረድተዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት መልዕክተኛ ፔካ ሃቪስቶ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት እያደረገ ያለውን የሰብአዊ ድጋፍ ህብረቱ እንደሚረዳ ጠቅሰው፣ ለዕርዳታ ፈላጊዎች የሰብአዊ ዕርዳታ በስፋት እንድዳረስ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንድቀጥሉ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ተከስተዋል የሚባለውን የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንዲያጣራ ጠይቀው ፤ የአውሮፓ ህብረት ስትራቴጅካዊ አጋርነት እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያሳያል።