የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በሚያልፍባቸው አራት ቦታዎች ተጨማሪ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት ጥናት እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በሚያልፍባቸው አራት ቦታዎች ተጨማሪ የገቢ ማስገኛ ፕሮጀክት ጥናት እየተካሄደ ነው
ሃምሌ 19/2010 የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በሚያልፍባቸው አራት ቦታዎች ላይ የተጨማሪ ገቢ ማስገኛ የፕሮጀክት ጥናት ስራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ። የኮርፖሬሽኑ ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ ለኢዜአ እንደገለጹት በሀገሪቱ የባቡር መሰረተ ልማት በብድር ገንዘብ የሚሰራ በመሆኑ ብድሩን ለመመለስ የሚያግዙ ተጨማሪ የገቢ ማስገኛ ልማቶችን እና ከተማዋ የሚያዘምኑ ትራንዚት ተኮር ልማት ለማከናወን ጥናት ተጀምሯል። የመጀመሪያው ምዕራፍ የትራንዚት ተኮር ልማትም በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር መስመር በሚልፍባቸው አራት የተመረጡ ቦታዎች እንደሚከናወን ጠቁመዋል። ለገሃር፣ ቅድስት ልደታ፣ አውቶብስ ተራ እና ዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ልማቱን ለማከናወን የተመረጡ ቦታዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። ልማቱ ከእነዚህ የባበቡር መስመር ጣቢያዎች ከ800 እስከ 1 ሺህ ሜትር ሬዲየስ እንደሚከናወን አቶ ደረጀ ተናግረዋል፡፡ በአራቱ የተመረጡ ቦታዎች ትላልቅ ሞሎች፣ ሱፐር ማርኬቶች እና ሌሎች አገልግሎቶችን በማቅረብ ገቢ የሚያስገኙ የልማት ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል። ወደ ልማት ስራው ሲገባ የግል አልሚዎችም ተሳታፊ እንዲሆኑ ሀሳብ መኖሩን ነው የጠቆሙት። የሚከናወነው ትራንዚት ተኮር ልማት ከከተማዋ ማስተር ፕላን ጋር የተጣጣመ፣ትራንስፖርትና ዘመናዊ ግብይትን የማስተሳሰር ዓላማ ያለው መሆኑን ነው ያብራሩት። የአዋጭነትና የአመችነት ጥናቶች እየተካሄዱ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ደረጀ ለዚህም ከተለያዩ የከተማ አስተዳደር መስሪያ ቤቶች እና ከምድር ባቡር የተውጣጡ 32 አባላት ያሉት ቡድን ወደ ስራ ገብቷል። ከአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ፣ የመልሶ ማልማት ፐረጀክት ጽህፈት ቤት፣ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ እና ሌሎችም የከተማ አስተዳደሩ ቢሮዎች ከኮርፖሬሽኑ ጋር በመሆን ጥናቱን እያካሄዱ መሆኑን አንስተዋል። በአዋጭነት ጥናቱ የወሰን ማስከበር፣ የካሳ ክፍያ ሁኔታ፣ የመሬት የዞታ እና የካርታ ስራዎች ይከናወናሉ። ኮሚቴው ጥናቱን በ2011 በጀት ዓመት መጨረሻ ያጠናቅቃል ተብሎ እንደሚገመት አቶ ደረጀ ጠቁመዋል።