ቀጥታ፡

የአድዋ ድል ኢትዮጵያን ለመከፋፈል የሚሰሩትን ለመመከት የሚያስችል የጀግንነት እርሾ ያለው ገድል ነው ... ዶክተር ሒሩት ካሳው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 3/2013(ኢዜአ) የአድዋ ድል በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ለመከፋፈልና ለመበታተን የሚሰሩ ቡድኖችን ለመመከት የሚያስችል የጀግንነት እርሾ ያለው ታሪካዊ ገድል ነው ሲሉ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሒሩት ካሳው ተናገሩ።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር "የአድዋ ድል ተምሳሌትነት" በሚል ርዕስ ያዘጋጀው "ቱባ ወግ" ወርሃዊ የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሄዷል።

በውይይት መድረኩ የአድዋ ድልን አስመልክቶ በታሪክና ስነ መለኮት ምሁራን የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጓል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የአድዋ ድል በተለያየ የሙያ መስክና የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው አንድ ሆነው ድል ያስመዘገቡት አኩሪ ታሪክ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከተለያየ ፈርጅ የተሰባሳቡት ኢትዮጵያዊያን ከኢጣልያን ጋር በነበረው ውጊያ ድል ለማድረግ የነበራቸው ተመሳሳይ የስነ ልቦና ዝግጁነትና መንፈስ የሚያስደንቅ እንደነበርም ነው ያስታወሱት።

የአድዋ ድል ተምሳሌትነት ከጊዜ ወደጊዜ ልክ እንደ ወይን እየጣፈጠ የመጣ የኢትዮጵያዊያን መገለጫ መሆኑንም የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል።

ጀግኖች አባቶችና እናቶች በአድዋ ጦርነት በከፈሉት ድል ኢትዮጵያን ጠብቀው ለትውልድ ማስረከባቸውንና የአሁኑ ትውልድም ከምንም በላይ ኢትዮጵያን በማስቀደም አሁን የገጠሟትን ፈተናዎች በጽናት ታግሎ በማሸነፍ ለዳግም ድል ራሱን ማዘጋጀት እንደሚገባው አስረድተዋል።

የአድዋ ድልን በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ ሥራ ልዩ ትኩረት እንደሚያሻውም የመድረኩ ተሳታፊዎች አመልክተዋል።

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው "የአድዋ ድል በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማማ ካወጡና የኩራት ምንጭ ከሆኑ ታሪካዊ ሁነቶች በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው" ብለዋል።

ድሉ ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለበት እንዲሁም ኢትዮጵያ ጦርነቱን እንዳታሸንፍ የተደረጉ ሴራዎች የከሸፉበት እንደነበረም አውስተዋል።

አፄ ሚኒሊክ በ1886 ዓ.ም የውጫሌ ስምምነትን አልቀበልም ካሉ በኋላ ኢትዮጵያና ኢጣልያን ለጦርነት ሲሰናዱ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ኢጣልያን ኢትዮጵያን ለማሸነፍ ከጦርነት በተጨማሪ በወቅቱ አፄ ምኒልክን ያኮረፉ ነገስታት ወደ ራሳቸው በማዞር ኢትዮጵያን ለማሸነፍ ሴራ ሸርበው እንደነበርና ይሄ ሀሳቧ ሳይሳካ በጦርነቱ መሸነፏን ነው ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ያስረዱት።

ሁልጊዜም ቢሆን ኢትዮጵያ በታሪኳ ጠላቶቿ ብዙ መሆናቸውን፣ ከራሷ አብራክ በመውጣትም ኢትዮጵያን የሚወጋ ወገኗ ፈተና ሆኖባት መቆየቱንና ይሄ ታሪክ አሁንም መቀጠሉን ረዳት ፕሮፌሰር አበባው ገልጸዋል።

የአሁኑ ትውልድ የአድዋ ድልን ታሪክ ከመዘከር ባለፈ አሁን ላይ ኢትዮጵያ እየገጠሟት ያሉ ፈተናዎችን ድል በማድረግ የራሱን ታሪክ መጻፍና አገሩን መጠበቅ እንዳለበትም አመልክተዋል።

የስነ መለኮት መምህር መጋቤ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያን የጋራ መግባባት በሚፈጥሩ በአድዋና እንደ አድዋ ካሉ ታሪካዊ ድሎች በመማር በአንድነት ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያን በታሪክ አድዋን ጨምሮ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ሌሎች ፈተናዎች እንድትሻገር ማድረጋቸውንና የአሁኑ ትውልድም ይህን እሴት የማስቀጠል ኃላፊነት እንዳለበት ተናግረዋል።

የአድዋ ድል ትውልድን ከትውልድ የሚያስተሳስር ታሪካዊ ድል መሆኑን የገለጹት ደግሞ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሒሩት ካሳው ናቸው።

ድሉ የመላው ኢትዮጵያዊያን አንድነት የታየበት እንደነበር ጠቅሰው፤ አገራዊ አንድነትን ጠብቀው ካቆዩ የህዝቦች ማስተሳሰሪያ ገመድ መካከል አንደኛው እንደሆነ ተናግረዋል።

"የአድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን የአሸናፊነት፣ የአዕምሮ ልዕልና እና የጀግንነት መንፈስ የታየበት የሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ድል ነው" ብለዋል።

አድዋ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ድል ከመሆኑ ባለፈ የኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊነት ጎልቶ የተንጸባረቀበት እንደነበረም ነው የገለጹት።

የአድዋ ድል በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን ለመከፋፋልና ለመበታተን የሚሰሩ ቡድኖችን ለመመከት የሚያስችል የጀግንነት እርሾ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ሒሩት፣ ኢትዮጵያዊያን አገራቸውን ከጠላት እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያዊያን የአድዋን ድል ታሪኮችና እሴቶች መጠበቅና መንከባከብ እንዳለባቸው ነው ያመለከቱት።

የዘንድሮው 125ኛው የአድዋ ድል በዓል "አድዋ የኅብረ-ብሔራዊ አንድነት አርማ" በሚል መሪ ቃል ይከበራል።

በዓሉ ከየካቲት 1 እስከ 30 ቀን 2013 ዓ.ም ወሩን ሙሉ የሚከበር ሲሆን የዘንድሮውን በዓል ለማክበር በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሚመራና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ምክር ቤት መቋቋሙ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም