የመንግስት ሰራተኞች ለምርጫ ቅስቀሳ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ደሞዛቸው ሳይቋረጥ በምርጫ መወዳደር ይችላሉ - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት ሰራተኞች ለምርጫ ቅስቀሳ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ደሞዛቸው ሳይቋረጥ በምርጫ መወዳደር ይችላሉ
የካቲት 3/2013 (ኢዜአ) የመንግስት ሰራተኞች የምርጫ በቅስቀሳ የዓመት እረፍትንና ሌሎች መንገዶችን በመጠቀም ደሞዛቸው ሳይቋረጥ በምርጫ መወዳደር እንደሚችሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለጸ።
ቦርዱ ለ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ አጠቃላይ ዝግጅት፣ በእጩዎች ምዝገባ መስፈርትና ሂደት፣ የድምጽ መስጫ ወረቀት ዝግጅት ላይ ከፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ዛሬ መክሯል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሚያቀርቧቸው እጩዎች መቅረብ ያለባቸው አስፈላጊ መስፈርትና ሰነዶች በዝርዝር ቀርበዋል።
በፌዴራልም ሆነ በክልል መንግስት ተቀጥረው የሚሰሩ ዳኞች፣ ዓቃቤ ህጎች፣ ወታደሮች፣ ፖሊሶች፣ ደህንነቶች ወይም ሌላ የፀጥታ አካል ሰራተኞች እና የምርጫ ቦርድ ሰራተኛ እጩ ተወዳዳሪ ሆነው መቅረብ እንደማይችሉ ተቀምጧል፡፡
የምርጫ እጩ ተወዳዳሪ ሆነው መቅረብ ከፈለጉ ለመመዝገብ ጥያቄ ሲያቀርቡ ከሚሰሩበት ተቋም የተጻፈ ስራ መልቀቃቸውን የሚገልፅ እና የመስሪያ ቤቱ ማህተም ያረፈበት ደብዳቤ ማቅረብ እንዳለባቸው ቀርቧል፡፡
በፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በእጩነት የሚቀርቡ የመንግስት ሰራተኞች ስራቸውን ሳይለቁና ደሞዛቸው ሳይቋረጥ ለምርጫው በእጩነት መቅረብ የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን አንስተዋል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በሰጡት ምላሽ የመንግስት ሰራተኞች በእጩነት የመቅረብ ጉዳይ በተደጋጋሚ ጥያቄ ሆኖ እየቀረበ መሆኑን አብራርተዋል።
በመሆኑ ዳኞች፣ ዓቃቤ ህጎች፣ ወታደሮችና ሌሎች ስራቸውን እያከናወኑ በፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍ ከማይችሉት ውጪ የመንግስት ሰራተኞች በእጩነት ስለቀረቡ የስራ ገበታቸው ላይ አይገኙም የሚል አሰራር አለመኖሩን አብራርተዋል።
ከካቲት 8 ጀምሮ በግልም ይሁን በፖለቲካ ፓርቲ አማካኝነት በእጩነት በመቅረብ የቅስቀሳ ጊዜው እስከሚቆይበት ግንቦት 4 ቀን 2013 ዓም ድረስ የቅስቀሳ ዘመቻውን ማድረግ ይችላል።
የምርጫ ቅስቀሳ ጊዜው ከሚወስዳቸው ወራቶች አንጻር ሙሉ የስራ ጊዜውን ትቶ በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ከተሳተፈ ደሞዝ ስለማይከፈለው የአመት እረፍት፣ በፖለቲካ ፓርቲው አማካኝነትና ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም ስራውን ሳይለቅ መወዳደር ይችላል ብለዋል።
የመንግስት ሰራተኞች በምርጫ ተሳትፈው ከተሸነፉ ወደ ስራቸው ሲመለሱ የሚገጥማቸውን ችግር ለመፍታት አቤቱታ የሚቀርብበትና የሚስተናገድበት መመሪያ እንደሚዘጋጅ ገልጸዋል።
ቦርዱ ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ 50 ሚሊዮን መራጮች ይኖራል ብሎ የገመተ ሲሆን እያንዳንዱ መራጭ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ለሚሰጠው ድምጽ 2 የድምጽ መስጫ ወረቀት ያስፈልጉታል።
ለዚህም እየተዘጋጀ ያለው የድምጽ መስጫ ወረቀት ናሙና ቀርቦ ፓርቲዎች አስተያየት ሰጥተውበታል።
ቦርዱ አጠቃላይ 100 ሚሊዮን የድምጽ መስጫ ወረቀት እንደሚያሳትም ገልጾ ከማጭበርበር፣ ከአቅምና ፍጥነት አንጻር በውጭ አሳታሚ ይከናወናል ብሏል።