ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ከግብ እንዲደረሰ እንደሚደግፉ የጋሞ እና ሃዲያ ዞኖች ነዋሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ከግብ እንዲደረሰ እንደሚደግፉ የጋሞ እና ሃዲያ ዞኖች ነዋሪዎች ገለጹ
አርባምንጭ/ሆሳዕና ፤ የካቲት 3/2013 (ኢዜአ)፡- የሀገሪቱን የለውጥ እንቅስቃሴ ከግብ እንዲደረስ በመደገፍ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የጋሞ እና ሃዲያ ዞኖች ነዋሪዎች ገለጹ።
ከሁለቱ ዞኖች የተወጣጡ ነዋሪዎች ዛሬ በአርባምንጭ እና ሆሳዕና ከተሞች የድጋፍ ሠልፍ አካሄደዋል።
በአርባ ምንጭ ከተማ በተካሄደው ሠልፍ ከተሳተፉት መካከል አርሶ አደር ተስፋዬ ግራ በሰጡት አስተያየት ጁንታው ባለፉት 27 ዓመታት በህዝቡ ላይ አድሏዊ በደል በማድረስ የበይ ተመልካችና ባይተዋር ሆኖ ቆይቷል ብለዋል፡፡
የለውጡ መንግስት ለኢትዮጵያ ህዝብ ብልጽግና ትልቅ ተስፋ ይዞ የመጣ በመሆኑ ህዝቡ ያጣውን ነፃነትና የአብሮነት እሴቶችን ማጣጣም ጀምረናል ብለዋል፡፡
ለውጡን በመደገፍም ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ50 ሺህ ብር በላይ ቦንድ በመግዛት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅሰው በቀጣይም ለማገዝ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያን ህዝብ ሲበድልና ሀብት ሲዘርፍ የቆየውን የጁንታው መወገድ ተገቢ መሆኑን ለመግለጽ የድጋፍ ሠልፉ ላይ መሳተፋቸውን የተናገሩት ደግሞ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ መሠረት ሽሽጎ ናቸው፡፡
ለእስራኤላዊያን ሙሴን እንዳዘጋጀ ሁሉ ፈጣሪ ለኢትዮጵያ ህዝብ ዶክተር አብይን በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ በማዘጋጀቱ ደስታዬ ወደር የለውም ብለዋል፡፡
የለውጡ መንግስት የሴቶችን እንባ በማበስ ከወንዶች እኩል መስራት እንደምንችል ያረጋገጠልን በመሆኑ የለውጡ ጉዞው እንድሳካ የበኩሌን እወጣለሁ ብለዋል።
ወጣት አሸናፊ ባንቲ በበኩሉ ሠላም የሁሉም መሠረት በመሆኑ በመደማመጥና መደጋገፍ የህዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ በሚደረገው እንቅስቀሴ በመሳተፍ እንደሚደግፍ ተናግሯል፡፡
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ ለህዝቡ ባስተላለፉት መልዕክት የለውጡ መንግስት የእውነትና የዕውቀት ፣የሠላምና የይቅርታ መንግስት ነው ብለዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይይ አህመድ በሳል አመራር ባለፉት ሶስት ዓመታት ለህዝቡ ልማት፣ብልጽግናና አብሮነት መጠናከር ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን አስረድተዋል።
በመንግስትና ህዝቡ ትብብር የሴራ ፖለቲከኞች አሠራር ዳግም ላይመለስ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ህዝቡ በቀጣይም ለአካባቢው ሠላምና ልማት ዘብ እንዲቆም አሳስበዋል፡፡
በተመሳሳይ ከሀድያ ዞን ወረዳዎች የተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሆስዕና ከተማ በመሰባሰብ ባካሄዱት ሠልፍ በተለይ የህዝቦችን የሠላም ጠንቅ የሆነው የህወሓት ጁንታ እንዲወገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለሰጡት ጠንካራ አመራር አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በየደረጃው መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን፣ እውነተኛ ዴሞክራሲ እውን እንዲሆንና በዲፕሎማስ መስኩም እያስመዘገቡት ያለው ውጤት አስደሳች በመሆኑ ቀጣይነት እንዲኖረው ከጎናቸው ሆነው እንደሚደግፉ ሠልፈኞቹ ባሰሙት መፈክር አስታውቀዋል።
ከሌሞ ወረዳ የመጣው ወጣት ታምራት አዳነ በሰጠው አስተያየት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል ህግ እንዲከበር ለሰጡት በሳል አመራር ያለውን አድናቆትና ድጋፍ ለመግለጽ በሠልፉ መሳተፉን ተናግሯል።
የሆሳዕና ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አየለች መኖ በበኩላቸው በሀገሪቱ እየተመዘገበ ያለው ለውጥ በገህድ የሚታይ በመሆኑ ይህን ለመደገፍ ሠልፍ መውጣታቸውን ገልጸዋል።
የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቲዎስ ሎምበሶ ለሠልፈኞቹ ባደረጉት ንግግር በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት በሀገሪቱ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ይህንን በመደገፍ ህዝቡ ላሳየው አጋርነት ምስጋና አቅርበዋል።
የዞኑ ህዝብ የበለፀገች ሀገር ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን መሆኑን ለመግለፅ በድጋፍ ሠልፉ ማረጋገጡን ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል።