“ሸገርን በአዲስ ገጽታ” የሚል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

59

አዲስ አበባ የካረተት 3/2021 (ኢዜአ) የመሬት ባንክና ልማት ኮርፖሬሽን አዲስ አበባን የሚያዘምን “ሸገርን በአዲስ ገጽታ” የሚል ፕሮጀክት ይፋ አደረገ።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሪት ሌንሳ መኮንን እንዳሉት ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት አዲስ አበባን በአዲስ ገጽታ ይቀይራል ተብሎ ይጠበቃል።

ከተማዋ ከዓለም አቀፍ ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያደርጋት መሆኑንም ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ በከተማዋ የፌዴራል መንግስት እየተጠቀመባቸው ባሉ የመሬት ይዞታዎች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚከናወን ነው።

ተቋማቱን መልሶ በማልማት ከተማዋን በሚመጥን መልኩ መልሰው እንደሚገነቡ ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል መንግስት ይዞታ ካለንበት ዘመን ጋር አብሮ የማይሄድ በመሆኑ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶችን የያዙ ይዞታዎች ያሏቸው ትውፊቶች ሳይነኩ ቅርስ በመጠበቅ የእድሳት ስራ ይከናወናል ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በከተማዋ ከሚሠሩ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች ጋር ተጣጥሞ የሚሰራ ሲሆን የመጀመሪያው ከቦሌ-ሽሮ ሜዳ እና ሁለተኛው ከለገሃር-ማዘጋጃ ቤት የሚያዋስኑ መሆናቸው ተገልጿል።

ለይዞታዎቹ አዲስ፣ ውብ እና የተለየ የዲዛይን ጽንሰ ሃሳብ በማቅረብ ሕብረተሰቡን ተሳታፊ የሚያደርግ ውድድር ለማዘጋጀት መታቀዱ ተገልጿል፡፡

በዚህም ከየካቲት 10 ጀምሮ በተቋሙ ድረ-ገጽ ለ30 ቀናት የአገር ውስጥ ዲዛይነሮች ውድድር ይደረጋል ተብሏል።  

በአዲስ መልክ የተቋቋመው ኮርፖሬሽኑ የፌዴራል መንግስት የመሬት ይዞታዎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውን ከፍ በማድረግ የማልማትና የማስተዳደር ኃላፊነት ይዞ ወደ ስራ መግባቱ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም