በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አመራር የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ በተቀናጀ አንድነት ማስቀጠል ይገባል -አቶ ደስታ ሌዳሞ

ሐዋሳ፣ የካቲት 3/2013 (ኢዜአ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ አመራር የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ በተቀናጀ አንድነት ማስቀጠል እንደሚገባ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስገነዘቡ።

ከክልሉ ከሁሉም ወረዳዎችና ከተሞች የተውጣጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ለመንግስታቸው ያላቸውን ድጋፍ ዛሬ ሀዋሳ ላይ ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ ገልጸዋል ።

ነዋሪዎቹ ከማለዳው 12 ሰአት ጀምሮ በሐዋሳ ዓለም አቀፍ ስታዲየም በመገኘት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አመራር በሀገሪቱ ለመጣው ለውጥና ለተመዘገቡ ውጤቶች ምስጋናና ዕውቅና ሰጥተዋል ።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ  በወቅቱ እንደገለጹት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው የለውጥ መንግስት ባለፉት 27 ዓመታት ህዝብን ያማረረውን የጭቆና አገዛዝ በመናድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘርፈ ብዙ ድል አስመዝግቧል።

በተደራጁ ሀይሎች  ሲመዘበር በነበረው የመንግስትና የህዝብ ሃብት ምክንያት ክፉኛ የተጎዳውን የሃገሪቱን ኢኮኖሚ በሃገር በቀል ዕውቀት እንዲያገግም በማድረግ የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ ከድሎች መካከል በዋናነት ተጠቃሽ መሆኑን አመልክተዋል ።

"የተጀመረው ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያን በማጠናከር የህዝቦችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የለውጥ መንግስቱን መደገፍ ይገባል" ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በነበረው የሰብአዊ መብት ጥሰትና አግባብነት በሌለው አገዛዝ የህዝብ ጥያቄ በማንሳታቸው በፖለቲካ ሃሳብ ልዩነታቸው ምክንያት ከእናት ሃገራቸው ለመሰደድ የበቁ ዜጎች ተመልሰው ሃሳባቸውን በነጻነት እንዲያራምዱ መደረጉ ሌላው  የተመዘገበው ለውጥ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል ።

የሲዳማ ህዝብ ለረዥም ዓመታት ሲጠይቅ የነበረው በክልል የመደራጀት ጥያቄን በመመለስ ዕውነተኛ ፌዴራሊዝም ዕውን እንዲሆን የለውጡ መንግስት ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ተናግረዋል፡፡

ላለፉት 27 ዓመታት ሃገሪቱን የመራው የጁንታው ቡድን ሲያራምድ የነበረው የሴራ ፖለቲካ ህዝብን በመከፋፈል ሀገርን ለመበተን ያለመ እንደነበር ያስታወሱት ርእሰ መስተዳደሩ የለውጡ አመራር በወሰደው በሳል እርምጃና በህዝቦች አንድነት ኢትዮጵያን ከጥፋት መታደግ እንደተቻለ አመልክተዋል ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሀመድ አመራር በሀገሪቱ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ ስኬታማ እንዲሆን በተቀናጀ አንድነት መስራት እንደሚገባ ርእሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል ።

የሲዳማ ክልል ብልጽግና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አብርም ማርሻሎ በበኩላቸው "በፖለቲካ፣በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስኮች የህዝቦችን መሠረታዊ ጥያቄዎች ከመመለስ ረገድ የለውጡ መንግስት ላስመዘገበው አመርቂ ውጤት ምስጋና ይገባል "ብለዋል፡፡

ሀገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል የተጀመረው የህዝብ ድጋፍና ንቅናቄን ማጠናከር የሁሉም ሀላፊነት ሊሆን እንደሚገባ ሀላፊው አመላክተዋል።

ከሰልፈኞች መካከል የሐዋሳ ከተማ ነዋሪ አቶ መስፍን ቂጤሳ በበኩላቸው  በዶክተር አብይ አህመድ አመራር በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት የመጣውን ለውጥ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል ።

"ሀገራዊ ለውጡን ጠንካራ መሰረት ለማስያዝና ለማስቀጠል ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጎን እንቆማለን" ብለዋል ።


"በዶክተር አቢይ አህመድ የሚመራው የለውጥ መንግስት በአጭር ጊዜ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ባደረጉት ጥረት ለተገኙ ስኬቶችና ለመጣው ሀገራዊ ለውጥ ምስጋና ለማቅረብና እውቅና ለመስጠት ሰልፍ ወጥቻለሁ" ያሉት ደግሞ ከይርጋለም ከተማ የመጡት ወይዘሮ ዘነበች ዶራ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም