የእርዳታ እህልና አልባሳትን በህገወጥ መንገድ ሲያጓጉዝ የተያዘ ተከሳሽ በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ

65
መቱ ሃምሌ18/2010 በኢሉአባቦር ዞን የሃሉ ወረዳ ፍርድ ቤት ለስደተኞች የተላከ የእርዳታ እህልና አልባሳትን በህገወጥ መንገድ ሲያጓጉዝ ተይዟል ያለውን ተከሳሽ በሰባት ዓመት ጽኑ እስራትና በገንዘብ መቅጣቱን የወረዳው ፍትህ ጽህፈት ቤት ገለጸ። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሰይፈዲን ሲራጅ እንዳስታወቁት ፍርድ ቤቱ ትናንት በዋለው ችሎት ቅጣቱን ያስተላለፈው ወንድም ክንዴ መንግስቱ በተባለ ተከሳሽ ላይ ነው። ተከሳሹ ኮድ 3- 87183 (አ.አ) በሆነ ኤፍ.ኤስ.አር የጭነት ተሽከርካሪ 100 ኩንታል ስንዴ 162 ዓይነት ብርድ ልብስ ጭኖ ከጋምቤላ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ የተያዘው ሰኔ 29 ቀን 2010 ዓ.ም ነው። ተሽከርካሪው ከህዝብ በደረሰ ጥቆማ በቁጥጥር ስር የዋለው በሃሉ ወረዳ ኡካ ከተማ መሆኑን የክስ መዝገብ ያስረዳል። "በንብረቶቹ ላይ የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) የሚል አርማ ያለበት ሲሆን እርዳታውም በጋምቤላ ክልል ለሚገኙ ስደተኞች የተላከ መሆኑን ፍርድ ቤቱ በማስረጃ ማረጋገጡን አቶ ሰይፈዲን ገልጸዋል። ግለሰቡ ፍርድ ቤት ቀርቦ ንብረቶቹን ከማያውቀው ሰው የገዛ መሆኑን ቢያስረዳም ህጋዊ የንግድ ሰነድ ማቅረብ ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛነቱን አረጋግጧል። ተከሳሹ በፖሊስና በአቃቤ ህግ የቀረበበትን ክስ ማስተባበል ባለመቻሉም ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የሀሉ ወረዳ ፍርድ ቤት በግለሰቡ ላይ የሰባት አመት ጽኑ እስራትና 150 ሺህ ብር እንዲቀጣ ውስኗል። በኤግዚቢትነት የተያዘው የእርዳታ ስንዴና በርድ ልብስ ደግሞ ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ትእዛዝ ሰጥቷል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም