ቀጥታ፡

ለእጩዎች ምዝገባ የሚያገለግሉ ሰነዶችና ቁሳቁሶች ዛሬ መሰራጨት ይጀምራሉ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3 ቀን 2013 (ኢዜአ) ለስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ለእጩዎች ምዝገባ የሚያገለግሉ ሰነዶችና ቁሳቁሶች ዛሬ መሰራጨት እንደሚጀምሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

ቦርዱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች ጋር በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ዙሪያ እየመከረ ነው።

በዚህ ወቅት ቦርዱ እንዳስታወቀው፤ ለምርጫ እጩዎች፣ ለመራጮችና ለድምጽ አሰጣጥ የሚያገለግሉ ሰነዶችና ቁሳቁሶች ዝግጅት ተጠናቋል።

ሰነዶቹና ቁሳቁሶቹ የሚሰራጩት በሦስት ምዕራፍ ተከፋፍሎ መሆኑን ያስታወቀው ቦርዱ፤ ለእጩዎች ምዝገባ የሚያገለግሉ ሰነዶችና ቁሳቁሶች ከዛሬ ጀምሮ መሰራጨት እንደሚጀምሩ አመልክቷል።

ለመራጮች ምዝገባና ለድምጽ አሰጣጥ የሚያገለግሉ ሰነዶችና ቁሳቁሶችም በቀጣይ እንደሚሰራጩም ገልጿል።

የየብስ፣ የአየርና ሌሎች የመጓጓዣ ዘዴዎችን በመጠቀም የሥርጭት ሥራው እንደሚከናወን አስታውቆ፤ “ስርጭቱን በክልልና በዞን ደረጃ ያሉ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ከምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች ጋር በመሆን ያከናውኑታል” ብሏል።

በስርጭት ወቅት በጉዞና በሚቀመጥበት ቦታ አስፈላጊውን ጥበቃ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ዝግጅት መደረጉም ተጠቁሟል።

በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልልን ሳይጨምር 673 የምርጫ ጣቢያዎች በመላ አገሪቱ ይገኛሉ።

የዞንና የምርጫ ክልል ጽህፈት ቤቶች በክልሎች መከፈታቸውን ከቦርዱ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም