የኤሌክትሪክ ኃይል በመቋረጡ ሥራችን ተስተጓጉሏል---- የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሪክ ኃይል በመቋረጡ ሥራችን ተስተጓጉሏል---- የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች
መተማ ሀምሌ 18/2010 የኤሌክትሪክ ኃይል ለሁለት ወራት መቋረጡ በሥራቸው ላይ ጫና እንዳሳደረባቸው በምዕራብ ጎንደር ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ የገንዳ ውሃ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ፡፡ በከተማው በመጠጥ ንግድ ሥራ የተሰማሩ አቶ አዳነ መንግስቴ እንደገለጹት በከተማዋ በሚኖሩበት ቀጠና ስምንት አካባቢ የኤሌክትሪክ ኃይል ከሁለት ወር በላይ ተቋርጦ በመቆየቱ በስራቸው ላይ ጫና ፈጥሮባቸዋል። እንደ ደንበኞቻቸው ምርጫ መጠጦችን አቀዝቅዘው ማቅረብ ባለመቻላቸው ደንበኞቻቸው እየሸሹና የእለት ገቢያቸው መቀነሱን የገለፁት አቶ አዳነ በእዚህም በሁለት ወራት ውስጥ ማግኘት የሚገባቸውን ከ2 ሺህ ብር በላይ ትርፍ ማጣታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል። "ችግሩ በእዚሁ ከቀጠለ የእለት ገቢን ታሳቢ በማድረግ የተጣለብኝን ግብር የመክፈል አቅም አይኖረኝም የሚል ስጋት ፈጥሮብኛል" ብለዋል ። በብረታ ብረት ሥራ የተሰማራው ወጣት ሰኢድ ይመር በበኩሉ በኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ስራውን በአግባቡ መስራት ባለመቻሉ በሁለት ወር ውስጥ ከምርት ሽያጭ ከ4 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማጣቱን ተናግሯል ። " የኤሌክተሪክ ኃይል ባለመኖሩ ከደንበኞቼ ጋር በገባሁት ውል መሰረት የታዘዝኩትን ምርት በወቅቱ ማቅረብ ባለመቻሌ ደንበኞቼ እንዲርቁኝ ምክንያት ሆኗል " ያለው ወጣት ሰኢድ ለቀጠራቸው ሰራተኞችም ደመወዝ መክፈል እየተሳነው መምጣቱን ተናግሯል ። "በከተማው የተለያዩ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል እያለ በእኛ አካባቢ ተቋርጦ መቆየቱ በእጅጉ ቅር አሰኝቶኛል" ያሉት ደግሞ በምግብ ንግድ ሥራ የሚተዳደሩት ወይዘሮ ያለምወርቅ እጅጉ ናቸው። ከተማው ሞቃታማ እንደመሆኑ የአየርና የምግብ ማቀዝቀዥ መጠቀም ባለመቻላቸው ምግብ እየተበላሸ ለኪሳራ እየተዳረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል። እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ ለከተማው አገልግሎት ጽህፈት ቤትና ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት መተማ አካባቢ ዲስትሪክት ችግሩን በተደጋጋሚ ቢያሳውቁም ምላሽ ማግኘት ባለመቻላቸው ተቸግረዋል። የገንዳውሃ ከተማ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊና ምክትል ከንቲባ አቶ አሸተ ደምለው ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በከተማው ቀጠና ስምንት ተብሎ በሚጠራውና በአካባቢው የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦ መቆየቱን ተናግረዋል ። "ለአካባቢው ሲያገለግል የነበረው ትራንስፎርመር በመቃጠሉ ችግሩ ተከስቷል" ያሉት ምክትል ከንቲባው ለመፍትሄው እስከ ክልል ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የመተማ አካባቢ ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ ከበደ በበኩላቸው የኃይል ተሸካሚ መሰሶዎች በነፋሰ ኃይል በመውደቃቸውና በትራንስፎርመር መቃጠል ምክንያት ከፊል የከተማው አካባቢ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡን ተናግረዋል ። ዲስትሪክቱ ከገንዳ ውሃ በተጨማሪ ለመተማ ዮሐንስ ከተማና ለቋራ ወረዳ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ የባለሙያ እጥረት እንዳለበት ገልጸው በእዚህ ምክንያት ችግሩን በወቅቱ መፍታት አለመቻሉን አስረድተዋል። በአሁኑ ወቅት ከዋናው መስሪያ ቤት ትራንስፈርመር ለማስመጣት ጥረት እየተደረገ በመሆኑ የተቋረጠው የኤሌክትሪክ ኃይል በአራት ቀን ውስጥ እንደሚስተካከል ተናግረዋል። ህብረተሰቡ ተገቢ ምላሽ አስከሚሰጥ ድረስ በትዕግስት እንዲጠብቅም ስራ አስኪያጁ አመልክተዋል።