ቀጥታ፡

የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የማህበረሰቡን አመለካከት ማሻሻልና ምቹ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር ይገባል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2 ቀን 2013 (ኢዜአ) የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ የማህበረሰቡን አመለካከት ማሻሻልና ምቹ የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር ይገባል ተባለ።

የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ላይ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ቅንጅቱ ከሴት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ጋር በምርጫው የሴቶች ተሳትፎና ያተኮረ ውይይት ዛሬ አካሂዷል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበራት ቅንጅት ፕሮግራም ማኔጀር ወይዘሮ መሰረት ዓሊ በወቅቱ እንዳሉት፤ ሴት የፖለቲካ በመገናኛ ብዙሃን ራሳቸውን እንዲያስተዋውቁና በፓርቲ አመራርና ውሳኔ ሰጪነት ዙሪያ ዓቅማቸውን ማሳደግ ያስፈልጋል።

“ሴቶች በመራጭነት በስፋት በመሳተፍ መብታቸውን እንዲጠቀሙ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ይከናወናሉ” ብለዋል።

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህርት ጽጌ ገብረመድህን ባቀረቡት ጽሁፍ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው አመለካከት መሻሻል እንዳለበት ገልጸዋል።

መንግሥትና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።

ሴቶች በበቂ መጠን በውሳኔ ሰጪነት ያለመሳተፋቸው ሴቶችን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ውሳኔዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ተናግረዋል።

ሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲያድግ ራሳቸውን ማብቃት እንደሚጠበቅባቸው መምህርት ጽጌ ገልጸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ ሴት የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት በሰጡት አስተያየት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን በበቂ መጠን በውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች የመመደብ ችግር እንዳለባቸው አረጋግጠዋል።

የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ካለፉት ዓመታት አንጻር መሻሻል እንደታየበት ገልጸው፤ ቀሪ ስራዎች እንዳሉም አመልክተዋል።

ሴት ፖለቲከኞች በውሳኔ ሰጪነት ቦታዎች ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ጫናዎችን ተቋቁመው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም