በስርአተ ጾታ ላይ የሚሰሩ ጥናቶች ሴቶችን ከማብቃትና የጾታ እኩልነት ከማስፈን አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው - ኢዜአ አማርኛ
በስርአተ ጾታ ላይ የሚሰሩ ጥናቶች ሴቶችን ከማብቃትና የጾታ እኩልነት ከማስፈን አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 2 /2013 (ኢዜአ) “በስርአተ ጾታ ላይ የሚሰሩ ጥናቶች ሴቶችን ከማብቃትና የጾታ እኩልነት ከማስፈን አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው” ሲሉ የሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ ገለጹ።
በብሔራዊ የፕላን ኮሚሽን የማዕከላዊ ስታቲክስ ኤጀንሲ ከዩ ኤን ውሜን ኢትዮጵያ እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በስርዓተ-ፆታ ስታትስቲክስና ኮቪድ-19 ርዕሶች ላይ የጥናት ሪፖርት ይፋ የማድረጊያና የማስራጫ መድረክ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የሴቶች ወጣቶችና ህጻናት ጉዳዮች ሚኒስቴርን ጨምሮ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲና ከዩ ኤን ውሜን እንዲሁም አጋር አካላት የተገኙ ሲሆን በስርዓተ ጾታና የኮቪድ-19 ተጽዕኖ ዙሪያ የተሰሩ ጥናቶቹ ቀርበዋል።
በዚህ ወቅት ንግግር ያደረጉት የሴቶች ወጣቶችና ህጻናት ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ “በስርአተ ጾታ ላይ የሚሰሩ ጥናቶች ሴቶችን ከማብቃትና የጾታ እኩልነት ከማስፈን አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው” ብለዋል።
በተለይም የሴቶችን የውሳኔ ሰጭነትና የአመራርነት ሚና ምን መምሰል አለበት የሚለውን አጀንዳ ለማሳካት ከፍተኛ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ጥናቶቹ በወጣት ሴቶች ላይ የሚሰሩ የማብቃት ተግባሮችን ለማሳካት መነሻ በመሆንና ምን መስራት አለብን የሚለውን ለመመለስ እንደሚረዱ ገልጸዋል።
የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር በ10 አመት ውስጥ የሴቶችን የውሳኔ ሰጭነትና የአመራርነት ሚና 50 በመቶ ለማድረስ ለጀመረው ስራ አጋዥ ሆኖ እንደሚያገለግልም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል በኮቪድ-19 ዙሪያ የተሰሩ ጥናቶች በቀጣይ መንግሥት ለሚያከናውናቸው የድጋፍ ስራዎች አቅጣጫ አመልካች እንደሚሆኑ ገልጸዋል።
“በወረርሽኙ ተጎጂ የሆኑትን በመለየት ከአጋር አካላት ጋር በተቀናጀ ሁኔታ ድጋፎችን ለማድረግ መንገድ ጠራጊ ናቸው” ብለዋል።
ይህንን ለማሳካት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ላደረገው አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።
በብሔራዊ የፕላን ኮሚሽን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ከ ዩ ኤን ውሜን ኢትዮጵያ እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተዘጋጁት ጥናቶች በስርዓተ-ፆታ ስታቲስቲክስና ኮቪድ-19ን ጨምሮ በአራት ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው።