የዱራሜ-ዳንቦያ-አንጋጫ-አመቾ ዋቶ-ሃላባ መንገድ ግንባታ ተጀመረ

81

አዲስ አበባ፣ የካቲት 2/2013 ( ኢዜአ) የዱራሜ-ዳንቦያ-አንጋጫ- አመቾ ዋቶ-ሃላባ የ65 ነጥብ 1 ኪሎ ሜትር የአስፋልት ኮንክሪት መንገድ ግንባታ ዛሬ በይፋ ተጀመረ።

የመንገድ ፕሮጀክቱ 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በጀት የተመደበለት ሲሆን ወጪው በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን ነው።

የመንገዱ ግንባታ ሶስት ዓመታት እንደሚፈጅም ተመልክቷል።

መንገዱ በከምባታ ጠምባሮ ዞን የሚገኙ አራት ወረዳዎችን እርስ በእርስና ከዋና መንገድ ጋር እንደሚያገናኝ በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር ፕሮጀክቱ በጥራትና በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ ለወሰን ማስከበር ሥራዎች ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው መንገዱ በዞኑ የሚመረቱትን ቡናና ቅመማ ቅመም ምርቶች በቀላሉ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እንደሚያስችል ገልፀዋል።

በተጨማሪም የዞኑን የቱሪዝም ፀጋዎች ለአገር ጥቅም ለማዋል ያስችላል ብለዋል።

ፕሮጀክቱን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮሚሽን የሚያከናውነው ሲሆን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ኮሚሽን ደግሞ የማማከር ስራውን ወስዷል።

በፕሮጀክቶቹ ማስጀመሪያ መርሃግብር ለመገኘት የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በቦታው ተገኝተዋል።

የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ የሲዳማና የኦሮሚያ ክልሎችን በማስተሳሰር የጎላ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳ ይኖራቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም