በአዲስ አበባ ህገወጥ ንግድን የመከላከል ሥራ የሚፈለገውን ውጤት አላስገኘም ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ህገወጥ ንግድን የመከላከል ሥራ የሚፈለገውን ውጤት አላስገኘም ተባለ
አዲስ አበባ ሀምሌ 18/2010 ህገ-ወጥ ንግድን የመከላከል ሥራው በሚፈለገው ደረጃ አለመከናወኑን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ። የከተማዋ ንግድ ቢሮ የ2010 ዓ.ም የሥራ አፈፃፀም ግምገማ በዛሬው ዕለት ተጀምሯል። የቢሮው ምክትል ሓላፊ አቶ ዳምጠው አበበ በዚሁ ጊዜ ባቀረቡት ሪፖርት "በከተማው የሚከናወነው ህገ-ወጥ ንግድን የመከላከል ሥራ ከዕቅዱ አንጻር ዝቅተኛ ነው።" በበጀት ዓመቱ ህገ-ወጥ ንግድን መከላከልና ወደ ህጋዊ አሰራር የማስገባት ሥራ የተሞከረ ቢሆንም ከችግሩ ስፋት አንፃር ስኬቱ በጣም አነስተኛ እንደነበርም ጠቅሰዋል። በከተማው የሚካሄደው መደበኛ ያልሆነ የንግድ እንቅስቃሴ የሚመራበት ፖሊሲና መመሪያ ፀድቆ በበጀት ዓመቱ ወደ ሥራ መገባቱን አስታውሰዋል። በዚህ መሰረት በከተማዋ መደበኛ ባልሆነ ንግድ የተሰማሩ ከ23 ሺህ በላይ ግለሰቦች መመዝገባቸውንም ገልጸዋል። ተመዝጋቢዎቹን ወደ ህጋዊ የንግድ ሥራ ለማስገባት በተደረገው ጥረትም ከ4 ሺህ በላይ ግለሰቦች ወደ መደበኛ የንግድ ሥራ ማስገባት መቻሉን ይገልፃሉ። ይህም ከተያዘው ግብ አንፃር በጣም አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ በከተማዋ የኮንትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድን ለመከላከል ግብረ ኃይል በማቋቋም በየደረጃው እንቅስቃሴ ቢደረግም ውጤቱ ዝቅተኛ እንደነበር ተጠቅሰዋል። ቢሮው ከራሱ ድክመት በተጨማሪ ኮንትሮባንድ ላይ ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል "ግልፅ የሆነ ሓላፊነት አልተሰጠውም" ያሉት አቶ ዳምጠው “እኛ ከህገ-ወጥ ንግድ ጋር አያያዝን ነው ለመከላከል የምንሞክረው” ሲሉ ተናግረዋል። ቢሮው ግልፅ የሆነ ሓላፊነት እንዲሰጠው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገራችን "በቀጣይ መፍትሔ ይሰጠዋል የሚል እምነት አለኝ" ነው ያሉት። አቶ ዳምጠው እንደገለፁት "የንግድ ቢሮው አደረጃጀትና የሰው ኃይል ህገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን ሳይጨምር በከተማዋ ያለውን ህጋዊ ነጋዴ እንኳን ለመቆጣጠርም አያስችልም።" ችግሩን ለመቆጣጠር የሚያስችል አደረጃጀት ለመፍጠርና የንግድ ሪፎርም ለማድረግ የሚያስችል ጥናት እንዲጠና በመወሰኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚሳተፉበት ጥናት በቀጣይ በጀት ዓመት ይካሄዳል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ በግንባታ ላይ ከነበሩት የገበያ ማዕከላት መሀከል በ2010 በጀት ዓመት 4 ቱ ግንባታቸው ተጠናቆ ለተጠቃሚዎች መተላለፋችውን በሪፖርቱ አስታውቀዋል። ግንባታቸው ተጀምሮ የተጓተቱና የቦታ ርክክብ የተደረገባቸው የገበያ ማዕከላት ግንባታ እንዲፋጠኑም ይሰራል ተብለዋል። በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ 16 ሺህ 189 ነዋሪዎች በ239 አዲስ የህብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅተው ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን የቢሮው ሪፖርት የሳያል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የህብረት ሥራ ማህበራት ኤጄንሲ በወረዳ ደረጃ በሰው ኃይል ያልተደራጀ በመሆኑ ችግሮች እየተፈጠሩ ናቸው ተብለዋል። ማህበራቱ ወደ ነዋሪው በሚያቀርቡት የመሰረታዊ ፍጆታ ሸቀጦች ላይ የስርቆትና የሚዛን ጉድለት በሰፊው እንደሚታይም ተገልፀዋል። በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በበጀት ዓመቱ 20 ኩንታል ስኳር፣ 2 ሺህ 464 ሊትር ዘይት እና 4 ነጥብ 5 ኩንታል ዱቄት አየር በአየር ሲሸጥ መያዙን የክፍለ ከተማው ንግድ ፅህፈት ቤት ሓላፊ አቶ ዮሃንስ በርሄ ባቀረቡት ሪፖርት በምሳሌነት አቅርበዋል። በከተማው የሚካሄደው የቁም አንስሳት ህገ-ወጥ ግብይት ቁጥጥርም አነስተኛ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በዚህም መንግስት ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ገቢ እያጣ መሆኑም ተገልጿል። በአሁኑ ወቅት በከተማው እየተካሄደ ያለው የንግድ ፍቃድ እድሳት ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው 5 ሺህ ከፍ በማለት ከ9 ሺህ በላይ ነጋዴዎች የንግድ ፍቃዳቸውን አሳድሰዋል። በአሁኑ ወቅት በከተማው 277 ሺህ በላይ ነጋዴዎች መኖራቸው የተገለፀ ሲሆን የሚበዙት የደረጃ “ሐ” ነጋዴዎች መሆናቸው ተገልፀዋል።