በምዕራብ ጉጂ ዞን በሴፍትኔት ፕሮግራም የታቀፉ 35 ሺህ የቤተሰብ አባላት የምግብ ዋስትናቸውን አረጋገጡ

36

ነገሌ፣ የካቲት 2/2013 (ኢዜአ) በምዕራብ ጉጂ ዞን በሴፍትኔት ፕሮግራም የታቀፉ 35 ሺህ የቤተሰብ አባላት እራሳቸውን በመቻል የምግብ ዋስትናቸውን አረጋገጡ፡፡

 ከነዚህም መካከል 288ቱ አባወራዎች በዞኑ ቶሬ ከተማ ጥር 30/2013 ዓ.ም.ተመርቀዋል፤ የቀሪዎቹ ምረቃም እንደሚቀጥል ተመልክቷል፡፡

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ወቅት የዞኑ ግብርና ልማት ጽህፈት  ቤት ምክትል ሀላፊ  አቶ  በድሉ  ገዛኸኝ እንዳሉት በዞኑ  አራት ወረዳዎች 71 ሺህ 600  የቤተሰብ  አባላት ላለፉት አምስት ዓመታት በፕሮግራሙ ታቅፈው ድጋፍ ሲደረግላቸው ቆይተዋል፡፡

ከእነዚህ ወገኖች ውስጥ 35ሺህ የሚሆኑት በአካባቢና ተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ መስኖ  ልማትና  የእንስሳት እርባታ ላይ ተሰማርተው  በመንቀሳቀስ   እራሳቸውን  በመቻል  ሀብት ካፈሩባቸው የሥራ ዘርፎች መካከል ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ በድሉ ገለጻ በዞኑ ገላና፣ ዱግዳ ዳዋ፣ ሶሮ በርጉዳ እና  መልካ ሶዳ ወረዳዎች   እነዚህ ወገኖች  ከድህነት ለመውጣት ባደረጉት ጥረት  የምግብ ዋስትናቸውን  ከማረጋገጥ  ሌላ በነፍስ ወከፍ ከ200 ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን 200ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ ሀብት አፍርተዋል፡፡

በፊት ያልነበራቸውን የቆርቆሮ ክዳን መኖሪያ ቤት፣ በግ፣ ፍየል፣  በሬ፣  የወተት  ላምና  ቋሚ ተክሎችን አንዳንዶቹ ደግሞ ወፍጮና የመሳሰሉ መለስተኛ የጎጆ ኢንዱስትሪዎችን አፍርተዋል ብለዋል፡፡

ቀሪዎቹ በሂደት ላይ እንደሚኙ አቶ በድሉ ገልጸዋል።

ለምረቃ ከበቁት መካከል በገላና ወረዳ የሜጣሪ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዋቆ ጎበና   በሰጡት  አስተያየት  ድርቅና የአካባቢ መራቆት በፈጠረው ጫና  በችግር  ያሳለፍኩት  ጊዜ  እንዳይደገም ያለድካም እየሰራሁ ነው ብለዋል፡፡

መንግስት ባደረገላቸው ድጋፍ  ጠንክረው በመስራት  እስካሁን ባካሄዱት እንቅስቃሴ እራሳቸውን ችለው የምግብ ዋስትናቸውን በማረጋገጥ ሀብት ማፍራት እንደቻሉ አስረድተዋል።

አቶ ዋቆ እንዳሉት በፕሮግራሙ ታቅፈው መስራት ከጀመሩ ወዲህ  አምስት  ልጆቻቸውን  በተለያዩ ኮሌጆችና ዩኒቨርስቲዎች እያስተማሩ ነው፡፡

የእህል ወፍጮ መትከላቸውን የተናገሩት አርሶ አደሩ አሁን ደግሞ የእርሻ ትራክተር ለመግዛት እየተዘጋጀሁ ነው ብለዋል፡፡

ሌላው የአከባቢው ነዋሪ ወጣት ታሪኩ ነጋሽ በበኩሉ  በሴፍትኔት ፕሮግራም  ታቅፎ   በግብርና ሥራ በመሰማራት ባለፉት ዓመታት ባደረገው እንቅስቅሴ ውጤታማ በመሆን አሁን ላይ አንድ ሚሊዮን 200ሺህ ብር ባንክ ተቀማጭ እንዳለው ተናግሯል።

በስኳር ድንች የጀመረውን የግብርና ስራ ወደ ቡና ልማት በማሸጋገር በሶስት ሄክታር መሬት ላይ ካላማው  የቡና ማሳ ምርት በመሰብሰብ ንግድ መጀመሩን ገልጿል፡፡

ወይዘሮ አዳነች ጎበና በሰጡት አስተያየት  የአራት ልጆች እናት እንደሆኑ ጠቅሰው  በችግር ምክንያት በፕሮግራሙ ታቅፈው ላለፉት አምስት ዓመታት ቡና ፣ እንሰትና አቦካዶ ቋሚ ተክሎችን እያለማሁ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም  በግና ፍየል በማርባት ኑሯቸው መሻሻሉን ተናገረዋል።፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም