ለሠላምና ለህዝቦች አንድነት መጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የሐይማኖት አባቶች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ለሠላምና ለህዝቦች አንድነት መጠናከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የሐይማኖት አባቶች ገለጹ
ደሴ፤ የካቲት 1/2013(ኢዜአ) ለአካባቢያቸው ሠላምና ለህዝቦች አንድነት መጠናከር ምዕምናኑን በማስተማርና በመምከር የድርሻቸውን እንደሚወጡ የሐይማኖት አባቶችና አባገዳ ገለጹ።
"የሐይማት ተቋማትና የአገር በቀል እውቀቶች ሚና ለሠላም ግንባታ" በሚል መሪ ሀሳብ ወሎ ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጀው የሠላም ኮንፈረንስ ዛሬ ተካሂዷል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ሀገረ ስብከት ዋና ፀሐፊ መላከ ሰላም ፈንታ አበራ በወቅቱ እንደገለጹት ለሀገር ሠላም፣ አንድነትና አብሮነት የሐይማኖት አባቶች ሚና የጎላ ነው፡፡
ትውልዱ የአባቶቹን ባህልና እሴት በትክክል ተረድቶ አንድነቱን በማጠናከር አብሮነቱን ማስቀጠል እንዲችል ለሠላምና ለህዝቦች አንድነት ግንባር ቀደም ሆነው በመስራት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡
''የሁሉም እምነት ስለሠላም አብዝቶ ያስተምራል'' ያሉት መላከ ሰላም ፈንታ በተቃራኒው ልዩነትን የሚሰብኩም በመኖራቸው ሀገር እንዳትረጋጋ እያደረጉ ነው ብለዋል።
ሌላው የቦረና ወረዳ እስልምና ጉዳይ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሐጅ ነስሩ አብዱል ከሪም በበኩላቸው ሀገር ከገጠማት ውስብስብ ችግር እንድትላቀቅ የሐይማኖት አባቶች ግንባር ቀደም ሆነን መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
በተለይ በሐይማኖትና ብሔር ስም የሚነግዱ ፖለቲከኞች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በየእምነት ተቋማችን ምዕምናኑን ማስተማርና መገሰጽ የዘወትር ተግባራችን እናደርጋለን ሲሉም ተናግረዋል።
የሐይማኖት ፎረሙን በማጠናከር ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ፖለቲከኞች እንጅ ህብረተሰቡ ተግባብቶና የጥንት ባህልና አብሮነቱን ጠብቆ ህይወቱን እየመራ ነው ብለዋል።
"የኢትዮጵያ አንድነትና የአብሮነት ወርቃማ ባህል ተጠናክሮ እንዲቀጥል የድርሻችንን እንወጣለን" ያሉት ደግሞ የከሚሴ ከተማ ነዋሪ አባ ገዳ አህመድ መሃመድ ናቸው፡፡
የአካባቢውን ህብረተሰብ በሐይማትና ብሔር ለመከፋፈል የሚሞክሩ ግለሰቦችን በመምከር፤ ምክር የማይቀበሉትን ደግሞ ለህግ እንዲቀርቡ በማድረግ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሃይማኖት አባቶች እምነቱ የሚለውን ብቻ በማስተማርና በመተግበር ሀገርን ከጥፋት መታደግ እንደሚገባ አባ ገዳ አህመድ ተናግረዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ሰላምና የህዝብ ደህንነት ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ አሊ ይማም በበኩላቸው ለቀጠናው ሠላምና መረጋጋት የሐይማኖት አባቶች የሚያደርጉት አስተዋዕጾ የጎላ ነው ብለዋል።
የሐይማኖት ፎረሙ እንዲጠናክር፤ አንድነትና ሠላም እንዲጎለብት ዞኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከአጎራባች ክልሎችና ዞኖች ጋር በመቀናጀት የህዝብ ለህዝብ ትስስሩ እንዲጠናክር ከመደረጉም ባለፈ ሁከትና ብጥብጥ በሚፈጥሩ ግለሰቦች ላይ እርምጃ በመወሰዱ በዞኑ አስተማኝ ሰላም መፍጠር መቻሉን አስረድተዋል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ ሥራ በተጓዳኝ ለአንድነትና ሠላም አበክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
በተለይ የአማራ፣ የኦሮሞ፤ የአፋርና የትግራይ ክልሎች አጎራባች ህዝቦች የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዲጠናከር በጥናት ታግዘው ውይይቶች እንዲካሄዱ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሀገር በቀል እውቀትም ከመንግስት ህጎች ጋር ተጣጥሞ ዘላቂና ችግር ፈቺ እንዲሆን በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በቀጠናው የሚስተዋሉ አለመግባባቶችንም የሐይማኖት አባቶችንና የመንግስት ተወካዮችን በማገናኘት ችግሮች በውይይት እንዲፈቱና አስተማማኝ ሠላም እንዲሰፍን የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በኮንፍረንሱ ከኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ፣ ደቡብ ወሎና ደሴ ከተማ የተውጣጡ የሐይማኖት አባቶች፣ ሀገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ አመራሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡