ቀጥታ፡

የመሠረተ ልማት ሥርጭት በመስፈርት መመራቱ በክልሎች ተመጣጣኝ ዕድገት ያመጣል - የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች

አዲስ አበባ የካቲት 1/2013 (ኢዜአ) የመሠረተ ልማት ሥርጭት በመስፈርት እንዲመራ መደረጉ በክልሎች ተመጣጣኝ የልማት ዕድገት ለማምጣትና የሕዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚያስችል የክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ገለጹ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በፌዴራል ደረጃ  በመሠረተ ልማት ስርጭት ጉልህ ሚና ያላቸው ተቋማት መሰረተ ልማቶቻቸውን የሚዘረጉበትን ግልጽ መስፈርት እንዲያወጡ አድርጓል።

ምክር ቤቱ የመሠረተ ልማት ተቋማቱ ለሚያከናውኑት ልማት የሥርጭት  መስፈርት  እንዲያዘጋጁ ያደረገው የሚዘረጉትን የመሰረተ ልማት አይነት መሠረት በማድረግ ነው።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ቀድሞ የነበረው አገራዊ የመሰረተ ልማት ስርጭት ግልጽ አሠራር የሌለውና በግለሰቦች ፍላጎት የሚመራ እንደነበር አስታውሰዋል።

ግልጽ አሠራር አለመኖሩም የሶማሌ ክልልን በመሠረተ ልማት ወደኋላ ቢያስቀርም የስርጭት መስፈርት ከተዘጋጀ በኋላ የህብረተሰቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ 15 መንገዶች መጀመራቸውን ገልፀዋል።

በመሰረተ ልማት ስርጭት የነበረውን የፍትሃዊነት መጓደል ከክልላቸው ተጨባጭ ሁኔ ጋር በማነጻጸር የገለጹት ደግሞ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ናቸው።

አሁን የስርጭ መስፈርት መዘጋጀቱ ጠቀሜታ እንዳለውና ወደፊትም አፈጻጸሙ እየተገመገመ የሕዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሀሊም አቡበክር በበኩላቸው "የመሰረተ ልማት ስርጭት መስፈርት ባለመኖሩ እንደ ሌሎች ክልሎች በልማት እኩል እንዳንጓዝ አድርጎናል" ብለዋል።

መንግስት ክፍተቱን ለማጥበብ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው ይህም ከሌሎች ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የልማት ደረጃ ላይ እንዲደርሱ አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል።

"ቀድሞ በነበረው አካሄድ የመሠረተ ልማቶች ስርጭት ፍትሃዊ እንዳልነበር መረጃዎች ያሳያሉ" ያሉት ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ እፀገነት መንግስቱ ናቸው።

ይህንንም ለማረም ምክር ቤቱ በመሰረተ ልማት ስርጭት ጉልህ ሚና ያላቸው ስምንት ተቋማት መስፈርት እንዲያወጡ ማድረጉን ገልጸዋል።

ተቋማቱ ከሚዘረጉት መሰረተ ልማት አንጻር ለክልሎች መስፈርት መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

ለመሰረተ ልማት ስርጭት ትልቅ ሚና አላቸው ተብለው መስፈርት እንዲያወጡ የተደረጉት ተቋማት የሳይንስና  ከፍተኛ  ትምህርት  ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ  መንገዶች  ባለስልጣን ፣  ኢትዮ-ቴሌኮም፣  የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ  ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የመስኖ ልማት ኮሚሽን፣  የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅትና  የኢንደስትሪ  ልማት  ኮርፖሬሽን  ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም