ከመተከል የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማገዝ የሁሉም ትብብር ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
ከመተከል የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማገዝ የሁሉም ትብብር ያስፈልጋል
የካቲት 1/2013(ኢዜአ)ከመተከል የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማገዝ ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባ ተገለጸ።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከመተከል ተፈናቅለው ቻግኒ ከተማ ተጠልለው ለሚገኙ 48 ሺህ ተፈናቃዮች የሁለት ሺህ 800 ኩንታል የስንዴ ድጋፍ አድርጓል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አመራሮች ተፈናቃዮቹ ያሉበት ሁኔታን ተዘዋውረው ከጎበኙ በኋላ ድጋፉን አስረክበዋል።
ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት በመጠለያ ጣቢያው የሚገኙ ህጻናት፣ ሴቶችና አቅም ደካሞች ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ ችግሩ ፈጥኖ የሚቃለልበትን መንገድ መቀየስ ይገባል።
ተፈናቃዮቹ በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ ከተሻሻለ ወደ ቀዬአቸው መመለስ እንደሚፈልጉ መናገራቸው የሚበረታታ መሆኑን ገልጸው፤ መንግስትም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከመተከልና አካባቢው ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያው የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ በቂ አለመሆኑን ገልጸው መንግስት አሁንም አስፈላጊውን ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዘላለም ልጃለም ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም ተፈናቃዮች በየጊዜው ወደ መጠለያ ጣቢያው እየመጡ በመሆኑ አስፈላጊው የምዝገባና የልየታ ስራ እስኪሰራ የድጋፍ መዘግየት እንደሚያጋጥማቸው ገልጸዋል።
መንግስት በመተከል ዞን ያጋጠመውን የጸጥታ ችግር ለመፍታት የተቀናጀ ግብረ ኃይል አደራጅቶ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።